Saturday, July 12, 2014

ለፀጋዬ አጭር ደብዳቤ

በካሌብ (ስንታየሁ) አለማየሁ


ለፀጋዬ አጭር ደብዳቤ
……………

አዎን አንተ ላንተ ኑረህ አታውቅም
የኛን ኑሮ ስትከረክም
የኛን እንክርዳድ ስታርም
የኛን አቃቅማ እሾህ ስትነቅል
ዝንጉ ነበርህ ለራስህ ውል
………
ታዲያ ምን ያደርጋል አባብዬ
ወዲህ የኛ ትንግርት ሌላ ነው
የኛ ጀብዳችን ልዩ ነው
ለሞቱልን መኖር አናቅ
ከጥበብ የተለየን
ከማየት የተጋረድን
ለማከበር የተፋፈርን
ነውር የማናውቅ ነውረኞች ነን
………………..
እና አባብዬ ልክ ነህ
ያንተ ውል ከቶ በእውንህ
በቁም ሳለህ በነፍስህ
ያስታውቅ ነበር ክታብህ
አንተን ዘንግተህ ለኛ
ሁሉን ኑሮ መኖርህ
ሁሉን ቅኔ መቃኘተህ
ሁሉን እይታ ማየትህ
ደፋር ነበር ብእርህ
ከሰይፍ አፋፍ የቆመ
እውነት ነበር ምናብህ
ለትውልድ ድህነት የታደመ
ንስር ነበሩ አይኖችህ
አጥንት ፈልቅቀው የሚያዩ
ግማድ ሀረጉን ሚተነብዩ
ደምን ከደም የሚለዩ
ፀጋዬ አንተ እንደስምህ ፀጋ ነበርክ
የህይወታችን አክሊል የብዕር ግርማ የተባልክ
………..
ፀጋዬ እኔ አንተን አይደለሁ
በምን ስንኝ በምን ቅኔ
አንተን ምን ብዬ እገልፃለሁ
ብቻ አልኩ ለማለት ብዬ
ስራህ ትዝታህ ከነፍሴ ከቁም አካሌ ባይጠፋ
ሌላውም ዝም እንዳይልህ ስምህ ከልቡ እንዳይጠፋ
ይቺን ስንኝ ሰደርኩልህ
ይድረስ ላንተ አባብዬ ባለህበት በሌላ አለም
መቸም ነፍስህ በገነት ናት ሌላ ስፍራ ለሷ የለም
ይኸው አንተን ከሸኘን በስቲያ
ማን ይናገርልን
ማን ባይናችን ይይልን
ማንስ በጆሯችን ይስማ
ማን በጣታችን ይፃፍልን
አንተ ነበርክ ፀግሽዬ
አመትባሉን ልቅሶውን
አብዮቱን ጥምቀቱን
ግርግሩን ጭርታውን
ክርክሩን ውይይቱን
ፍቅርና ጥላቻውን
እኛን ሆነህ የኖርክልን
ታዲያን ዛሬ ብቻችንን የብዕር ዋግምት ሲቆጋን
ማንም ሀዬ አላለን
አንተም አትመለስም
መንፈስክም ከትውልዱ የለም
ብርታትክም ከኛ ዘንድ የለም
እና ስማኝ አባቴ
ፀግሽ ልንገርህ ካንጀቴ
ዛሬ እኛ ብዙ ሺ እጦት
ብሶት ሆይታ አለብን
ከዕጦቱ ሁሉ እጦት ግን
አንተን እጦት ነው የባሰን
ጭንቃችንን ከጭንቀቱ
ምጣችንን ከምጡ
ቀላቅሎ የሚኖርልን
………….
እናም ይድረስ ላንተ ባለህበት
የእውነት ዛሬም ከልብህ
ከውስጥ ከአንጀት ከደምህ
ትወደን እንደሆነ
መንፈስክን በደህና መንፈስ ጠቅልለህ ላክልነ
ብርታትክን በደህና ብርታት አጅለህ ስደድልነ
ድፍረትክን በደህና ድፍረት ጠምጥመህ አኑርልነ

እውነትክን በሙሉ ሚስጥር ጥበቡን ሹክ በለነ፡፡

No comments:

Post a Comment