Thursday, December 12, 2013

ስምና ሁናቴ
…………….
በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

ስም ያው ብዙ ጊዜ መጠሪያ ነው ፣ አንዳንዶቹ ወላጆች ከሁኔታዎች ጋር እያመሳሰሉ ያወጣሉ ፣ አንዳንዶቹ አፋቸው ላይ የመጣውን ደስ ያላቸውን ስያሜ ይሰጡበታል፡፡ በእኛ ሀገር በተለይ አፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ በሆነበት አካባቢ ስሞቻችን አንዳንድ ግዜ ከአባት ስም ጋር ተገጣጥሞ ትርጉም እንዲሰጥ ፣ እንዲገጥም ፣ መልክት እንዲያስተላልፍ ፣ አንዳንድ ጊዜ ደሞ ተረት መተረቻም ቅኔ መቀኛም ያደርጉታል፡፡ 
ለምሳሌ እኛ ሰፈር የነበረ አቶ አወቀ የሚባል ሰውዬ ፣ የልጆቹን ስም ከሱ ስም ጋር እንዲገጥም አድርጎነው ያወጣሁ፣ መቅደም አወቀ፣ መስጠት አወቀ፣ ወ/ሪት ማታለል አወቀ፣ መሳቅ አወቀ፣ እና ወላጆች አንዳንዴ ሳስበው ለነሱ ከነሱ ጋር የሚሄድ ስም ይሁን እንጂ ምንም አይነት ቃል ይሁን በቃ ዝም ብለው ይለጥፉብናል ፣ በቃ ‹‹ምናባቱ እኔ ለፍቼ ለማሳድገው ደሞ የስም ባለመብት ደሞ እሱ ሊሆን ነው›› ብለውና ‹‹በገዛ ልጃችንና በገዛ ቋንቋችን ማን ነኪ አለን›› ብለው የሚያወጡ ነው እሚመስለው ፣ እውነቴን እኮ ነው! አስቡት እስቲ ማታለል አወቀ ብሎ ስም ማውጣት እስቲ ምን ይሉታል ፣ በቃ ‹‹ ከኔ ስም ጋር ይግጠም ብያለሁ ይግጠም!›› ይላል አቶ አወቀ ፣ እሱ ሳይሰማ እዛ ቤት ለተወለደው ልጅ ፣ ወንድም ይሁን ሴት ስም አይወጣለትም፣ አቶ አወቀ ‹‹በዘራችን እማይገጥም ስም አውጥተን አናቅም›› እያለ እሚኮፈስ ፣ ያወጣው ስም ለወጣለት ልጅ ይመርበትም አይመርበት ፣ ከሱ ስም ጋር ብቻ ገጥሞ ካየ በቃ ‹‹እንዲህ ናቸው የአውቄ ልጆች አ!›› እያለ በየመንገዱ ጉራውን እሚነዛ ሰው ነው፡፡ ወይ የኛ ሰው ብሎ ብሎ እሚኮራበት ቢያጣ በልጁ ስም መንቀባረር ጀመረ! አይ እኛ አስቂኞቹ……
ወደሌላ ስም እንለፍ አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ፣ ሊያልቅ ሲል ገነነ እሚባሉ መከረኛ ፣ የሆኑ የአባታቸው የአረፍተ ነገር መስሪያ የሆኑ የሚመስለኝ ፣ አንዳንዴም የወላጆጃቸው የማስታወሻ ደብተር ወይም ዲያሪ የሚመስሉኝ ልጆች አሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ወቅት ጠብቀን ለልጆጃችን ስም እንደምናወጣ ሁሉ ፣ ወቅት ጠብቀን ደሞ ብንቀይርላቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ ፣ እኚህ መከረኛ ልጆች በደርግ ጊዜ ፣ በዚያ የኢሀዲግና የደርግ ጦርነት ወቅት ፣ በዚያ በተፋፋመ ጊዜ በመወለዳቸው ፣ ፈርዶባቸው አቶ ገነነም ስም አወጣጥ ይችላሉ መቸም! አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ እና የመጨረሻው የደርግ-ኢሀዲግ ጦርነት ግዜ የተወለደውን ደግሞ ሊያልቅ ሲል ገነነ ብለው ስም አውጥተዋል፡፡ ዛሬ ታዲያ አቶ አብዮት ስሙን አይወደውም ፣ ሆ እውነቱን እኮ ነው ፣ አስቡት እስቲ አብዮት ብሎ አቶ ፣ አሁን በዘመነ ዲሞክራሲ እና በዘመነ ሰላም ሰው ልጁን አብዮት ብሎ ይሰይማል ፣ እሺ ቆይ ያኔስ ጊዜው ነው ፣ ልጁን አብዮት ብሎ ቢሰይም ግድ የለም ፣ አሁን እሺ ያ ዘመን አልፏል አይደለ እንዴ ምናለበት ስሙን ለምሳሌ ከአብዮት ወደ እውቀቱ ፣ ሰላሙ ፣ ፍክክር ምናምን እያሉ ቢያወጡለት እንዴ እውነቴን እኮ ነው ፣ መቸም ከአባት ስም ጋር እንዲገጥም አደል እሚፈለገው ፣ ይኸው ይገጥማል፡- እውቀቱ ገነነ፣ ሰላሙ ገነነ ፣ ፉክክር ገነነ እያሉ መጥራት ይቻል ነበር ታዲያ ምን ያደርጋል የኛ ሰፈር አባቶች አይሰሙም አቦ!
አቶ ገነነም ልክ እንደ አቶ አወቀ ሁሉ ‹‹በህግ አምላክ ካወጣሁልህ ስም ውልፍች ትልና›› እያሉ በቃ ልጆቻቸው በስማቸው አብዮት አብዮት እየሸተቱና እየከረፉ ተሳቀው በመኖር ላይ ናቸው፡፡
በእርግጥ ስለ ስም ስናወራ በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በተለይ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገሮችም ስም ከሁኔታና ከተግባር ጋር ተያይዞ ይወጣል፣ ለምሳሌ ጀርመኖች ሸማኔውን ሸማኔ ፣ እቃ ሻጩን እቃ ሻጭ ብለው የሚጠሩበት አጋጣሚ አለ፣ ሌሎችንም እንዲሁ ብዙ በስራቸውና በሁኔታቸው የሚያወጡበት አጋጣሚ አለ ፣ ማለትም ለምሳሌ ሸማኔውን ዌቨር ፣ ሻጩን ሴለር ምናምን እያሉ ይጠራራሉ ማለት ነው ፣ ይሄን ሰምቼ ታዲያ ዘወር ስል እትዬ ብርጣሉና እማማ ወርቂቱ ግብ ግብ ተያይዘው ደረስኩ ፣ ምነው ምን ሆነው ነው ፣ ምን አጋጫቸው ? ስል የእትዬ ብርጣሉ ልጅ ነው ነገረኛው የእማማ ወርቂቱን ልጅ የሸማኔ ልጅ ብሎ ተሳድቦ ነው አሉኝ! እማማ ወርቂቱ እትዬ ብርጣሉን ‹‹እንዴት ብትንቂኝ ነው በይ ብለሽ ብለሽ ልጅሽን ልከሽ የሸማኔ ልጅ ብለሽ ልጄን እምታሰድቢው እረ!›› ብለው ነጠላቸውን ጥለው ገጠሙ፣ ታዲያ አያችሁ ልዩነት? በጀርመን ሽምንና ከተከበረ ስራም አልፎ የተከበረ ስም ሆኖ ሳለ ወዲህ በኛ ሀገር ግን ንቀት ካዘለ ስድብ ተቆጥሮ ጎረቤት እና ዘር ማንዘር ያጣላል ጉድ ነው ሀበሻ!
ብቻ ግን እንተወውና ሰው መቸም እንደባህሉ ነው እሚኖረው ፣ እንደጀርመኖች ደፋር ሆነን ሸማኔውን ሸማኔ ብለን መሰየም ባንችልም ፣ ባይሆን እንደው ገና ለገና ከአባት ስም ጋር እንዲገጣጠም ብለን እባካችሁ ያልሆነ ስም አናውጣ ተመልከቱ ፡- ሳራ ከች አለ ፣ ቀፋፊው ፊቱ፣ አረግርግ ቆመጡ ብሎ ስም ምን ይሉታል እስቲ!
ሳራ ከች አለ! ብሎ ስም ! መጀመሪያውኑ ከች አለ ብሎ ስም አያስቅም ደረሰ እሚለውን ስም በቦሌ ብሄረሰብ ቋንቋ እ…ከች አለ! ወይ መንቀባረር ከዛ እንዳይገጥም ይሁን እንዲገጥም አይታወቅም በቃ ልጆቻቸውን የሆነ ቃል እየለበጡባቸው ወላጆች ይደበራሉ! አሀሀሀሀ ….አስቂኝ ነገር ነን…ሳራ ከች አለ ከምንል ቢቻል አንዴ ሆኗል መቸም የአባቷን ስም መቀየር አንችልም እንጂ ከች አለ እሚለውን ደረሰ በሚል የሀገሬን ለዛ ያለው ቃል መጠቀም ጥሩ ነበር ግን ምን ዋጋ አለው! አንዴ ሆኗል እሱ ነገር ግን ልጂቷን ለዚህ ስም አጋልጦ ከመስጠት ፣ ከአባቷ ስም ጋር መገጣጠሙ እንደ ህገ መንግስቱ የማይናድ ህግ ከሆነ ምን ይደረጋል ፣ በቃ ሳራ ከማለት ስሰራ ፣ ሳነብ ፣ ወይ ደሞ በዛው በለመዱት በቦሌኛቸው ኬክ ስበላ ፣ ፊልም ሳይ ፣ ጌም ስጫወት ምናምን እሚሉ ስሞችን ሰጥቶ ከሳቅን አይቀር በደንብ መሳቅ ነው፡፡ ከዛ በቃ ከአባቷ ስም ጋር ሲገጣጠም ስሰራ ከች አለ፣ ኬክ ስበላ ከች አለ፣ ፊልም ሳይ ከች አለ! አሁን እስቲ ይሄ ስም ነውን ሆ! ወሬ አረግነውኮ በቃ! መቸም አንዴ በዚህ ሀገር ስም ማውጣት ማለት አረፍተ ነገር መመስረትና አማርኛ ፔረድን እድሜ ልክ መሳተፍ ነውና!....ምን ማድረግ ይቻላል አብረን እንሳቃ…….
አንዴ እንዲሁ በስም ጉዳይ ከሆነ መንገድ ላይ ካገኘሁት ሰው ጋር እያወራን እያለ ፣ አሱ እራሱ በስሙ ሁሌም እንደሚበሳጭ ነገረኝ ፣ ምነው ምን ሆንክ ፣ ማን ነው ስምህ ስል ጠየኩት….
እረ ተወው እሱን አሲቂኝ ነው ስሜ ፣ ካልጠፋ አማርኛ እስቲ በናትህ ብሎ ድንገት እንባው ጥርዝዝ አለ…እንዴ ቆይ እንጂ ይሄን ያህል ምን ቢሆን ነው ስምህ እረ ደስ አይልም እንዳታለቅስ ብዬ በግድ አባብዬ ጠየኩት ስሙን ነገረኝ፣ ስሙ ገፊው ኮስትሬ ነው፡፡ እና አንተ ካስጠላህ አታስቀይርም እንዴ ምን አጨናነቀህ ስለው ፣ ‹‹እሱ አይደለ እንዴ እሚደብረው›› ብሎ ቀጠለ ፣ ‹‹አያቴ የማስቀየር መብቴን ይዞት ሞቷል›› አለኝ ፣ እንዴ እንዴት አይነት ነገር ነው ፣ ጭራሽ የሰው መብትም ይዞ መሞት ይቻላል እንዴ! እረ ይቺ ጉደኛ አገር ብዬ ፣ እንዴት ነው ግን አያትህ የማስቀየር መብትህን ይዘውት የሞቱት ፣ መብት አይደለም የሰው ልጁ ልብሱንና ወርቁን ሳይቀር ሲሞት እዚህ ትቶ አይደለ እንዴ እሚቀበረው አልኩት፣ ‹‹አይ አንተ ጥሩ ብለሀል›› ብሎ ቀጠለ ‹‹ይሄ እኮ ባይን የማይታይ የአደራ ቃል ነው ፣ በቃ ማንም የልጅ ልጄ እኔ ስም አውጥቼለት ፣ ደስ ሳይለው ቀርቶ አስቀይሮ አያውቅም፣ እና አደራ ብየሀለው ልጄ ፣ ካስቀየርክ በአዲስ ስምህ ትሞታለህ ፣ ኑሮ አይቀናህም ፣ ብሎ እርግማንም ትንቢትም ቀላቅሎ ነው ነገሮኝ የሞተው ስለዚህ ቃሉን ብሽር ትንቢቱና እርግማኑ የሚደርስ ስለሚመስለኝ እፈራለሁ ፣ እና ይኸው አሁን ማንም ገፌ ፣ ገፎ ፣ ገፊቲ እያሉ ቁልምጫ አይሉት ስድብ እየተጠራሁበት እገኛለው›› ብሎ አጫወተኝ፡፡
አንዳንዴ ደሞ የሚያስቀው ነገር፣ መቸም አንዴ ስለስም ከተነሳ ብዬ ነው ፣ በቃ የሆነ የውጭ ሀገር ስም ነገር ከሆነ ደስታችን አይጣል ነው፣ እነ ዮሀንሶች ጆን ሲባሉ ደስታቸው አይጣል ነው! ፣ እነ ሮቤል ሮበርት ሲባሉ ይፈነድቃሉ! ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ብዙ ብዙ ግን ለምን ፣ አንዱ ጓደኛዬ ምርር ብሎት ያደለውማ ሪሀና ራውል ይባላል እኔ አለው እንጂ ለቁልምጫ እንኳን እማይመች አረገሀኝ እሚል ስም ይዤ ወይኔ! ሆ ብቻ የሆነ ብዙ አስቂኝ ነገር አለው ፣ በመጨረሻ ግን የበኩሌን ልምከራችሁ ፣ አንዳንዴ እኮ ከወጣትም ምክር መቀበል ብፁእነት ነው ፣ እና እኔ እምለው ምን መሰላችሁ ስም ስታወጡ በተለይ ለወላጆች የናንተን ታሪክ እንዲወክል ብቻ አታስገድዱ እሺ ግን ይሄም ይሁን ነገር ግን ልጁ ሲያድግ የመቀየር መብት ይኖረው ዘንድ ህገ መንግስታችሁን ወይንም ህገ ስማችሁን ተቀያሪ ፍሌክሴብል አድርጉት እንጂ ባለፈ ትውልድ እና መንግስት አሰያየም የወጣውን ስም ተሸክሞ የመኖር ግዴታ ያለበት ልጅ የለም፡፡በዚህ እግር ምናለበት መጥፋት የሌለባቸው ስንት ሺህ ቋሚ ቅርሶች አሉን አይደለ እንዴ ፣ እነሱን ካፈረስክ ወዮልክ ብላችሁ ለምን ቃል አስገብታችሁ አትሞቱም!.....አበቃሁ፡፡

No comments:

Post a Comment