Monday, October 14, 2013

ሀገር ማለት….

ሀገር ማለት….

                                                  በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

ይህ ግዜና ይህ ሰአት፣ ይህ ወቅትና ይህ አመት በጣም ልዩ ነው ፣ ቃል ብቻ እሚገልፀው ሳይሆን አይን አይቶ የመሰከረው እጅግ ውብ ነገር ነው እየታየ ያለው፡፡ እግር ኳሱ ይዞት የመጣው አዲስ ቅኝት አለ፣ አዲስ ውበት አለ፣ ውስጠትን ማንነታችንን የገለፀበት ቋንቋ አለ፡፡ ሰሞነኛ እንዳይሆን እንጂ ይህ ያሁት ነገር፡- 
አገሬ  ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
እያለ እሚቀጥለውን የገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥም አስታወሰኝ፤ ከዚህ ግጥም ስንኝ "ቀለም የሞላበት" እምትለውን እንድዋስ ያስገደደ ሰሞንና ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡ በቃ ይቺ ናት ሀገሬ ብዬ ደግማ ሳትጨልም በካሜራ ቀርጨ እንዳስቀምጥ ያስገደደ ሰሞን፣ ከማላውቀው ከማያውቀኝ ነገር ግን እጅግ ውብ ከሆነ እትዮጲያዊ ጋር በስሜት ያስተቃቀፈ ሰሞን፣ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችን ቋንቋ አንድ ያደረገ ሰሞን፣ እስትንፋስና ደማችንን እንዲሁም ቀለማችንን አንድ ያደረገ ሰሞን መሆኑን ሳስብ ድጋሜ ሌላ ግጥም ትዝ አለኝ፣ ምስጋና ለባለቅኔዎቻችን ይሆንና ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ "ሀገር ማለት የኔ ልጅ" ከሚለው ግጥሙ መሀል ለዚህ ወግ የሚመቸኚን ስንኝ ልዋስና እንዲህ ይላል፡-
ሀገር ማለት የኔ ልጅ 
ሀገር ማለት ቋንቋ ነው በአንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት፤
አማርኛ ኦሮሞኛ  አፋርኛ ቅማንተኛ፤
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ፣ ብለው የማይፈርጁት 
የኔ ልጅ፣
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞውና ሲዳማው  ጉራጌኛሽን ባይሰማ፤
ያልገባው እንዳይመስልሽ  ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስታወት፤
ሲከፋሽ ትሽሽጊበት  ሲደላሽ ትኳኳየዪበት 
እናም ባንደበት ሳንናገረው በገሀድ እንዳየነው፣ በጆሮ ሳንሰማው በህሊናችን እንዳደመጥነው፣ በብሄርብሄረሰብ ሳንገደብ ባንድ ቋንቋ እንዳወራነው፣ ህዝብንና ትውልድን ባንድ ሰንደቅ እንዳስተሳሰረ፣ የሁለንተናችን መስታወት እንደሆነም፣ ስንደሰት በሰንደቅ እንደተሸፋፈንን ሲከፋንም በሰንደቋ መሸሸጋችንን ከዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በላይ፣ ከዚህ ግጥም በላይ እኛ በገሀድ ያየነው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለብሰነው በሰነበትነው አረንጓዴ፣ቢጫ ቀይ ከለር ውስጥ የሀገር ፍቅር ይታይ ነበር፣ ተሰብስበን በቆምንበት ሰአት አንድነትን መናፈቃችን ይታይ ነበር፣ በፈገግታችንንም ይሁን  በሀዘናችን መሀል ፍፁም የሆነ የሀገር ስሜት ይታይ ነበር፣ ለኔ አረንጓዴ ቤጫ ቀዩን ቀለም ስንቀባ ፣ በልባችን ፍፁም የኢትዮጲያዊነትን ፣ የዐንድነትን ደም ፣ የፍቅርን ቃል ኪዳን ፣ የባንዲራን አደራነት ስልጣን የተቀባን ነው የመሰለኝ፣ ለኔ ተቃቅፈን በየጎዳናው አንድ ላይ ባንድ ቀለም ስንሄድ፣ ስንቦርቅና ስንደሰት፣ ስናዝንና ስንከፋ የዋልነው፣ የቀድሞውን ማንነታችንን፣ የአንድነት እትብታችንን ለማደስ ነው፣ ጌዜና ወቅት ያቋረጠውን ፍቅራችንን ለመጠገን ነው እላለው፣ ሺ ውበት፣ ሺ ቋንቋ፣ እልፍ ልዩነቶች በትልቁ አንድ ሆነው የታዩበት፣ የጠፉ ማንነቶች ከየጓዳው የተመዠረጡበትን ቀን ነው እየኖርን ያለነው፡፡
ሰዎች የተከፋፈለ ማንነታቸውን ፣ ጥለት የተቀባ ታሪካቸውን በተለያዩ ምክኒያቶችና ሰበቦች ያድሳሉ፣ ከነዚህም መካከል እንዲህ አይነቱ ብዙሀኑን የሚያሳትፍ ኳስና መሰል ጨዋታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለኔ ለዘጠና ደቂቃ ከሚለጓት ኳስ እና ቡድኑ ከሚያመጣው ውጤት በላይ በኛ በተመልካቹ ላይ የሚያመጣው ታላቅ ሰጋዊ ወመንፈሳዊ ነጥብ አለ፣ ዛሬ እኮ ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ማንን እናሰልፍ ማን ይጫወት የማያውቀው ሰው እንኳን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ስላየ ብቻ ጥቅምት 3ትን ሲጠባበቅ ነበር፣ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ቡድን ስለተባለ ብቻ አንዳች ህመምና ጭንቀትን ሁሉም ዳር እስከዳር ተጨንቋል፣ ዛሬ ይህ ህዝብ እልፍ ቁስሉንና ህማሙን በሰንደቁና በቀለሙ ሸፍኖታል፣ ስንት ሺህ መነጣጠሎችንና መነፋፈቆችን በዚህች ድቡልቡል ኳስ ሰበብ ድል አድርጓል፡፡ በዚህች ኳስ ምክኒያት የተነጣጠለ ትውልድ ተገናኝቷል፣ የተደበቀ ህያው ፍቅር አደባባይ ወጥቷል፡፡ ውበታችንንና አንድነታችንን ያሳየነው እኮ ሜዳ ውስጥ ለናይጀሪያዎቹ ብቻ አይደለም ይልቁንም ከምንምና ከማንም በበለጠ ለራሳችን እና ለእኛው ወገን፣ እንዲህ መፋቀር እየቻልን ለተጣላን፣ እንዲህ አንድ ነበርንን ስሜት ለራሳችን መልክት ያስተላለፍንበት፣ ያገር ፍቅር በግድ እሚነጥቁንን እምቢኝ አሻፈረኝ ያልንበት መድረክ ጭምር እንጂ ለኔ አዲስ አበባ ስቴድየም እግር ኳስ ሜዳ ብቻ ሆኖ አልዋለም፡፡
እንግዲህ ሀገር ማለት እንዲህ ከአይን በላይ ጠልቀው የሚያዩት ከሆነ፣ ከጆርም በላይ የሚያደምጡት ከሆነ፣ ከጥርስም በላይ በውስጥ የሚስቁበት ከሆነ፣ ከቋንቋም በላይ ቋንቋ ያለው ከሆነ እንዲሁ እንደጀመርን ቀደምት ማንነታችንን የምናሳይበትና የምናድስበት ይሁን እላለሁ አሁንም ይቅናሸ ሀገሬ፡፡


No comments:

Post a Comment