Saturday, April 13, 2013

poet legends

ሃገሬ

አገሬ ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
አገሬ ቆላ ነው፣ ደጋ ወይና ደጋ
እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ።
አገሬ ተራራ ሸለቆ ረባዳ
አገሬ ጅረት ነው ገደልና ሜዳ።
ውሸት ነው በበጋ ጸሃይ አትፋጅም
ክረምቱም አይበርድም፣
አይበርድም፣ አይበርድም።
አገሬ ጫካ ነው
እንሰሳት አራዊት የሚፈነጩበት
በወጥመድ ሳይገቡ ሳይነካቸው ጠላት።
እዚያ አለ ነጻነት።
በሃገር መመካት፣
በተወላጅነት፣
በባለቤትነት፣
እዚያ አለ ነጻነት።
አገሬ ሃብት ነው።
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎ ክትፎ ስጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው፣ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ።
ጠጁ ነው ወለላ
ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ።
እህሉ ጣዕም አለው እንጀራው ያጠግባል
በዓሉ ይደምቃል፣
ሙዚቃው ያረካል፣
ጭፈራው ዘፈኑ ችግርን ያስረሳል።
እዚያ ዘመድ አለ።
ሁሉም የናት ልጅ ነው፣
ሁሉም ያባት ልጅ ነው፣
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር
ባለጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ ሲቸገር” ።
ገነት ነው አገሬ።
ምነው ምን ሲደረግ !
ምነው ! ለምን ! እንዴት !
ዘራፊ ቀማኛ ምቀኛ ወንበዴ
ጥርኝ አፈር በጁ ስንዝር ወሰን አልፎ
የተቀደሰውን ያፍሪቃ ላይ ደሴት
ባያገኝ ለማርከስ ጠላት ይመኝ እንዴት።
እምቢኝ አሻፈረኝ !
አሻፈረኝ እምቢ !
መቅደስ ነው አገሬ፣
አድባር ነው አገሬ።
እናትና አባት ድኸው ያደጉበት
ካያት ከቅደመ አያት የተረካከቡት
አፈር የፈጩበት፣
ጥርስ የነቀሉበት።
አገሬ ዓርማ ነው የነጻነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ።
እሾህ ነው አገሬ፣
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ።
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት።
ለምለም ነው አገሬ፣
ውበት ነው አገሬ፣
ገነት ነው አገሬ።
ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ።
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ።
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ።

ገብረ ክርስቶስ ደስታ
 
 
 
የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን



የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ
ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ፡፡
እና ትንፋሼ አልሆነሽም፥ ሆኜብሽ መራር መካሪ
ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ፣
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት፥ ጉስቁል ልሳንሽን ነክሳሽ
ክንድሽን ካዘለ ቅርስሽ፥ መጠላለፍ ሲሆን እጣሽ
ከእንግሊዝ የሞት አማልክት፥ መተናነቅ ሲሆን ድርሻሽ
መልመጥመጡ፥ መሽቆጥቆጡ፥ መስሎሽ ድንገት የሚያዋጣሽ
የኔ እውነት ሆነብሽ ዕዳሽ ፡፡  …..
ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፥ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ
መች ትተርፊያለሽ ኢትዮጵያ፥ ሕዋስሽ አብሮኝ ካልሠራ
አንገትሽ ብቻ መቅደላ፥ አፋፍ ወጥታ ብታበራ
የቀረው ሠራ-አከላትሽ፥ በየጥሻው ተዘርሮ
ከአባት በወረሽው ንፍገት፥ ነብዞ ደንዝዞ ተቀብሮ
ባጉል ወጌሻ ታጅሎ
እጅና እግርሽ ታሽቶ ዝሎ
እኔን ለጥንብ አንሳ ጥሎ፤
ከደቀቀ ከደከመ፥ ክንድሽ አልነሣ ካለ
ሞት እንጂ ለኔስ ምን አለ?.....
ሆኖም ጐስቋላ አልምሰልሽ፥ የሚያዝንልኝ አልፈልግም
ጠላትሽን በክንድሽ እንጂ፥ በእንባሽ ወዝ ባላሸንፍም
የልቤን ፍቅር በሰተቀር፥ እማወርስሽም ውል የለኝ
የኮሶ ሻጭ ልጅ ደሃ ነኝ፡፡ …..
ደሞም ያላንቺ የለኝና
ድሌም የተሰፋ ጐሕ ባይሆን፥ ከሞት ጋር ትግል ነውና
ከዚህ ሌላ ትእዝብት ውረሽ፥ ሳይነጋ እንዳስመሸሽብኝ
ጊዜና ትውልድ ይፍረደን፥ ሳልነቃ እንዳስረፈድሽብኝ፡፡
ያም ሆኖ ለራስሽ እንጂ ለኔ ከቶም አታልቅሺ
አንቺ ነሽ እንባ እምትሺ፤ …..
የእምነትሽ መተሣሰሪያ፤ ውልሽ ለተላቀቀብሽ ላንቺ ነው እንባ እሚያሰፈልግሽ፡፡
አዎን፥ ይኽን እወቁልኝ፥ ምስክር ሁኑኝ ሰማዕታት
ለሷ ነው እንባ የሚያስፈልጋት፡፡
ከጠላቶቹ ጭብጥ ውስጥ፥ ትንፋሼን በጄ ስነጥቃት
ሞቴን ከመንጋጋቸው ውስጥ፥ መንጭቄ እኔው ስሞታት
ላገሬ ብድር ልከፍላት
የነፈገቺኝን ፍቅር፥ በራሴ ሞት ልለግሳት!.....
ያኔ ነው እንባዋ የሚያጥራት፡፡
ሰለዚህ ለራስሽ እንጂ፥ ልቅሶሽ ለኔ ምን ሊረባ
ብቸኛ ምሬት ነው ኃይሉ፥ ወኔ መሰለቢያው ነው እንባ፡፡
እና ለራስሽ እዘኚ
እንጂ ከቶ ለኔ እትባክኚ፡፡ …..
ይልቅስ ተረት ልንገረሽ፥ የተላከ ከእንግሊዝ ዘንድ
እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፥ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፥
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ፡፡ …..
ዳዊት እንዲያ በበገናው፥ ማልቀስ ማላዘን መያዙ
ይኽ የጐልያድ ውላጅ፥ ቢበዛበት ነው መዘዙ
ምንጩ እንደአሽን እየፈላ፥ አገሩን ምድሩን ማንቀዙ
ቸግሮት ነው፥ መጋፈጡ፥ ከስንቱ መወናጨፉ
በባላንጣው ሳቢያ ምክንያት፥ የራሱን ወገን ማርገፉ፡፡ …..
ታድያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ፥ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፥ ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅነነት የሚያሳፍረን፥ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነንምንድነን?
አሜከላ እሚያብብብን፥
ፍግ እሚለመልምብን፥
ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች፥ ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር
ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ፥ ከቶ ያልተበራየን መከር
ምንድነንምንድነን እኮ?
አረጋዊውን ባንቀልባ፥ ከምንሽከም እንኮኮ
ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፥ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ
እንደ ወዶ ገባ ወደል፥ መጠለሉን ከሴት ታኮ …..
ካቃተን፥ ምንድነን እኮ?.....
አየሽ እንቺ እማማ ኢትዮጵያ፥ አየሽ አንቺ እናት ዓለም
ቃል የእምነት ዕዳ ነው እንጂ፥ ያባት የናት እኮ አይደለም፡፡ …..

ያም ይቅርና መርዶ ላርዳሽ፥ ስሚው እኔ እንደሰማሁት
እርም በልተሽ ከምትቀሪ፥ ስሚው ገብርዬንም ጣሉት፡፡ …..
እስቲ እንግዲህ በይ ፍረጂኝ፥ ከእንግዲህ እኔ ፍሬ አላይም?
ዘርቶ መቃም ወልዶ መሳም
አባባል ለኔ አይባልም?
እስቲ ገብርዬን መሰል ዘር፥ ፍሬው ከቶ አይለመልምም?
እኔስ ዘር ዘራሁ አልልም? …..
ምነው ፍንጭትክን ገብርዬ፥ ያን ፍንጭትክን አጨለሙት
እንደ ሬት ልግ አከሰሉት
እንደ ኮሶ አስመረሩት? ......
ከጡቶችሽ እቅፍ ነጥቀው፥ ከማኅፀንሽ ፍቅር ቆርጠው
እውነትን ሲገሉ እንዲህ ነው፥ ፈገግታውን አጨልመው፡፡
እስቲ እባክህን ገብርዬ፥ የዛሬን እንኳ ስቀህ ሙት
በዕድል ጥቀርሻ እንደአጀሉት
እንደ ወላድ ጣውንት ጡት
አርማ ጉሳ እንደቀለሙት
ፈገግታህን አያጥቁሩት፡፡
እምቢ በላቸው ገብርዬ፥ በአባት ሤራ እንዳስገዘቱት
በመሃላ እንዳሳገዱት
የነፍሰህን ጮራ ብርሃን፥ ከገጽህ እንደቀበሩት
ዘለዓለም ላያጨልሙት
ወንድምዬ እምቢ በላቸው፥ የዛሬን እንኳ ስቀህ ሙት፡፡ …..
ያለፈ ጥረታችንን፥ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ፥ ያልሞከረነው ነው እሚቆጨኝ፡፡
እና በኔ ይሁንብህ፥ መጣሁ፥ ስቀህ ተቀበለኝ
እኔም ላዋይህ አድምጠኝ …..
እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፥ እጅ ተይዞ ሊወሰድ
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ፡፡ …..
                              ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
                              እሳት ወይ አበባ

 
 
 
ሀገር ማለት የኔ ልጅ - በዶ/ በድሉ ዋቅጅራ
 
------------------
ሀገር ማለት ልጄ፣ ሀገር ማለት፣
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ የተወለድሽበት አፈር፤
እትብትሽ የተቀበረበት ቀድመሽ የተነፈሽው አየር፤
ብቻ እንዳይመስልሽ።
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
አገር ውስብስብ ነው ውሉ።

ሀገር ማለት ልጄ
ሀገር ማለት ምስል ነው ፣በህሊና የምታኖሪው፤
ከማማ መህጸን ከወጣሽበት ቀን ጀምሮ
በጠባሽው ጡት፣ ወይም ጡጦ
በዳህሽበት ደጃፍ፣ በወደቅሽበት ፈፋ፤
በተማርሽበት ትምህርት ቤት፣
በተሻገርሽው ዥረት
በተሳልሽበት ታቦት ፣ወይ በተማፀንሽው ከራማ
በእውቀትሽና በህይወትሽ፣
በእውነትሽና በስሜትሽ
የምትቀበይው ምስል ነው በህሊናሽ የምታኖሪው፤
ስትወጅ ሰንደቅ ታደርጊው፡፡
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው።

ሀገር ማለት የኔ ልጅ
ሀገር ማለት ቋንቋ ነው በአንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት፤
አማርኛ ኦሮሞኛ አፋርኛ ቅማንተኛ፤
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ፣ ብለው የማይፈርጁት

የኔ ልጅ፣
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞው ሲዳማው ጉራጌኛሽን ባይሰማ፤
ያለገባው እንዳይመስልሽ ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስታወት፤
ሲከፋሽ ትሽሽጊበት ሲደላሽ ትኳኳየዪበት

የኔ ልጅ
አያት ቅም አያትሽ ፣ሰላም ሲሆን ከወልቂጤ አድማስ ማዶ ሸቅጦ፣
ሲያቀና ወረቱን፤
ለእኔና ለአንቺ መኖሪያ፣ ሲያቀና ቀዬና ቤቱን፤
ሀገር ጠላት ሲደፍራትም፣ ጦሩን ሰብቆ እየፎከረ፤
ከኦሮሞው ከትግሬው፣ ከአፋሩ ከወላይታው፣ . . . ከሁሉም የጦቢያ ልጆች
አጥንቱን እየማገረ፤
ሀገር ይሉት መግባቢያ ፣ሰንደቅ ይሉት መለያ ሲያቆይልሽ፤
በጉራግኛ ማትገልጭው፣ በጎጥ የማትገድቢው፣ ስንት አለ ታሪክ መሰለሽ!

እና የእኔ ልጅ፣
ለዚህ ነው ሀገር ይሉት ቋንቋ፣ ላንቺ የሚያስፈልግሽ፤
ከወልቂጤ አድማስ ማዶ፣ ለተሳሰረ ታሪክሽ፤
ከወልቂጤ አድማስ ማዶ ለተወጠነው እድገትሽ።
እና ልብ በይ ልጄ ! ሀገር ማለት ቋንቋ ነው፣ ባንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት።

ከሁሉም በላይ ልጄ
ተፈጥሮ ከቸረው በረከት የላቡን ፍሬ የሚበላ፤
ሀገር ማለት ወገን ነው፣ የእኔ የምትይው ከለላ።
ትመኪበት ጥሪት፣ ትደምቂበት ብርሃንሽ፤
የሰብዕናሽ ግማሽ ውል ፣ወገን ነው ማሕተምሽ፡፡
ዜጋው ነው ልጄ ሀገርሽ።

መሬትማ የእኔ ልጅ፣
በእምነትሽና እውቀትሽ፣ ከልለሽ ካላበጀሽው፤
ለእድገትሽ ውጥን ካልሆነ ፣ለተስፋሽ ካልተመገብሽው፤
መሬትማ ባዳ ነው፣ ላለማው የሚለማ፤
ለተስማማው የሚስማማ።
ዥረቱም ግድ የለውም ቦይ ለማሰለት ይፈሳል
ተራራውም ደንቆሮ ነው ለቦረቦረው ይበሳል።
መሬቱ አደለም የኔ ልጅ፣ እድርተኛው ነው ሃገርሽ፤
ስትቸገሪ ታድጎ፣ ስትታመሚ አስታሞ፣ ስትሞቺ አፈር ሚያለብስሽ።
በእጅሽ ያለ ብሩህ ጽጌ ሰው ነው ልጄ ሀገርሽ፤
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ።

እና የኔ ልጅ፣
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ።
------------
ታህሳስ 1999 ለልጃችን ኬርአለም
ፍካት ናፋቂዎችመድብል
/ በድሉ ዋቅጅራ
 
 
 
መልክአ እናት - በዕውቀቱ ስዩም
----------
ሰላም ለኪ እናታችን
ባለሽበት እንዳለሽ
አንቺ የተባረክሽ ነሽ
ሰላም ለዓይኖችሽ
ከጭስ ጋራ ለሚሟገቱ
ከእንቅልፍ ጋር ለተፋቱ
ተቅበዝባዥ ፍጡር ሆኜ ኑሮዬን ከምገፋ
ምነው እንባሽን በሆንኩ
ከዓይኖችሽ ስር እንዳልጠፋ፡፡
ሰላም ለከንፈሮችሽ ትላንት ለማውቃቸው
ዛሬ ለምናፍቃቸው
ውዳሴ ክብር ምርቃት
ጭብጨባ ሙገሳ ሽልማት በተረፈበት ቀዬ
ምነው 'ንቺን እርግማን - ይናፍቃል ጆሮዬ
ከሌሎች ውዳሴና ክብር እልፍ ጊዜ የተሻለ
ለካ 'ርግማንሽ ውስጥ እናትነትሽ አለ፡፡
ሰላም ለጣቶችሽ
ለሰዎች የቀረቡ፣ ከራስሽ ግን የራቁ
መስጠት መለገስ እንጂ መቀበልን ለማያውቁ
ሰላም ለኪ!
ባለሽበት እንዳለሽ፡፡
-------------
በዕውቀቱ ስዩም፣ የግጥም ስብስብ፣ 2001 .

2 comments:

  1. ታድያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ፥ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
    አመንኩሽ ማለት የማንችል፥ ፍቅራችን የሚያስነውረን
    ዕዳችን የሚያስፎክረን
    ግፋችን የሚያስከብረን
    ቅነነት የሚያሳፍረን፥ ቂማችን የሚያስደስተን
    ኧረ ምንድነን? ምንድነን?
    አሜከላ እሚያብብብን፥
    ፍግ እሚለመልምብን፥
    ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች፥ ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር
    ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ፥ ከቶ ያልተበራየን መከር
    ምንድነን? ምንድነን እኮ?
    አረጋዊውን ባንቀልባ፥ ከምንሽከም እንኮኮ
    ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፥ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ
    እንደ ወዶ ገባ ወደል፥ መጠለሉን ከሴት ታኮ …..
    ካቃተን፥ ምንድነን እኮ?.....
    አየሽ እንቺ እማማ ኢትዮጵያ፥ አየሽ አንቺ እናት ዓለም
    ቃል የእምነት ዕዳ ነው እንጂ፥ ያባት የናት እኮ አይደለም፡፡ …..a real idea even for this time generations

    ReplyDelete
  2. yeeeeesssssssssssssss..............

    ReplyDelete