በካሌብ
አለማየሁ
አንችን መሳይ ቆንጆ ለኔ የሰጠኝ፣
መውደዴን ወደድኩት ያንች ያረገኝ፣
እያለ እየዘፈነ ነው ሙሉቀን፣ እኔ በሀይገር አውቶብስ ተረጋግጨ፣ እኔም ሰው ረግጨ ፣ በቃ
ተደራርበን ማለት ይቻላል መኪናው እየበረረ ነው፡፡ትከሻየ ላይ የሆነ ሰው እጅ አለ፣ ጉልበቴን አንዱ ተጭኖታል፣ክንዴን አንዷ እጮኛዋ
አስመስላ ግጥም አርጋ ይዛኛለች፣አንገቴን ደግሞ ይቅርታ መያዣ አጥቼ ነው ብሎ አንዱ ሌባ ይመስል ሲሊዬን አንቆ ይዞኛል፡፡አሁን
ኪሴ ውስጥ ማንም ቢገባ አልሰማም፣ምክኒያቱም አይደለም ኪሴን ቀርቶ አንገቴን ታንቄ ተይዤ ነፍሴንም ለማዳን ከባድ ነው፣ በግድ እንደምንም
እረ ባክህ ብዬ ለምኜ ጉሮሮዬን አስለቀኩ፣ መተንፈስ ጀመርኩ፣በጥቂቱ በተከፈተ መስኮት አጮልቄ አላፊ አግዳሚውን ማየት ጀመርኩ፡
አንዱ ቁጭ ብሎ ጫማ ያስጠርጋል፣አንዱ እህል ያሸክማል፣አንዱ ሱቅ ቁጭ ብሎ ገዢ ተርቧል፣ዘወር ስል ደግሞ ”እራበኝ አይን የለኝ
አይነ ስውር እርዱኝ ተማፀኑኝ” እሚል ልብ የሚነካ ድምፀት ሰማሁ፣ዘወር ስል ለታክሲና ለአውቶቢስ የተሰለፈው ህዝብ ይርመሰመሳል፣መለስ
ስል ደግሞ ያለነሱ ሰው ያለም ያልመሰላቸው ጥንዶች ተቃቅፈው ዎክ ያደርጋሉ፣ በእያንዳንዷ ስንዝር እርምጃ ይሳሳማሉ፣ይላላሳሉ፣ይጎራረሳሉ
ብል ነው የሚገልፃቸው፡፡ የገረመኝ ግን እኔና እኔን መሰል የመኪና ተሳፋሪ አይኑን ይጥልባቸው እንደው እንጂ እንዲያ በየመንገዱ
ሲላላሱ ማንም ልብ ያላቸው የለም በቃ አለማችን በሩጫ ላይ ነች፡ሊስትሮዎቹ እንኳን ስራ አልፈቱም እገረኛው ሰው ሁሉ በሀሳብ ነው
እሚሄደው፣ በቃ መንቀዥቀዥ ፣መሯሯጥ፣ እረፍት የለም፣ቀልብ የለም፣እፎይታ የለም፣አሁን ጭራሽ ባሰባቸው በስመ አብ እጆቹ አንዴ ወደ መቀመጫዋ፣ አንዴ ወደ ሀር ዞማ ፀጉሯ እሚሄዱበት ግራ ጠፍቷቸው
ከላይ እታች ይወራጫሉ፣ እኔ አስሬ ምራቄን እየዋጥሁ በጣም ተመስጨ አያለሁ፣የኔንም ምራቅ አዋዋጥ ሌላው ተመስጦ ይይ አይይ እኔ
አላውቅም ብቻ አይን ማረፍ ካለበት በዚያ ሰአት ትክክለኛው ቦታ ጥንዶቹ ላይ ነው፡፡ አፍጥቼ ወደነሱ ምን ጉድ ይፈጠር ይሆን ዛሬ
እያልኩ መኪናውም እንዲሁ ሊደራርበን ሰው ከመጥራቱ ባላረፈ ጥንዶቹንም አልፈናቸው ባልሄድን ካሁን አሁን በሩን ዘግቶ እንደተለመደው
’’ሳበው ሳበው” ብሎ ባልሄደ፣ወይ እንደተለመደው መንገዱ ለዛሬ ተዘጋግቶ
በቆየ እያልሁ እያሰብኩና ጥንዶቹ ላይ አፌን ከፍቼ ሳለሁ ትከሻዬ ላይ እጁን ጣል አድርጎ ’’አባቱ ሂሳብ’’ አለኝ ወያላው፡፡ ከላይ
በመጀመሪዬ እንደገለፀኩት ገና መኪናው ውስጥ ገብቼ እንደተቀመጥኩ የሙሉቀን ቆንጆ ዘፈን ተከፍቶ ነበር ወጌን አቆሜ ወደ ውጭ ስመለከት
የቆየሁት፣ ወያላው ሂሳብ ጠይቆኝ ከከፈልኩ በኋላ አቅሌን እንደገና ወደ ዘፈኑ መለስኩ፡
አንችን መሳይ ቆንጆ ለኔ የሰጠኝ፣
መውደዴን ወደድኩት ያንች ያረገኝ፣
ይላል እግዚሀሩ ለኔ የሰጠኝ ግን እንዲህ ሙሉቀን
እንደሚገልፃት አይደለችም ፣ ከንፈሯ እንጆሪ፣ ሀር የመሰለ ፀጉር፣ እሷ በሌለችበት ውሀ ውሀ እሚያሰኝ ምናምን አይደለችም፡፡ የኔይቱ
ሰርክ በጣቷ መሀል እምታውለው ሲጃራ ከንፈሯን ጥቁር ሊፒስቲክ የተቀባች ያስመሰላት፣ ፀጉሯ ወዲያና ወዲህ ተበታትኖና ተንጨባሮ የሆነ
የሰአሊ ንድፍ እሚመስል ነው፣ታዲያ ሙሉቀን ምናለ የውጭ ቁም አካልን ብቻ ማቆላመጥ ወደደ የኔይቱ እንግዲህ እንዳልኳችሁ ዘፋኝ አይዘፍንባትም
፣ ባለቅኔም አይመርጣትም ፣ የኔይቱ ጥቂት ውበት አላት ከተባለ ውስጧ ነው አሱንም ሲሻት ትዘባርቃለች፣ እንደምስቅልቅል ፀጉሯ አመሏም
ምስቅልቅል ይላል፡፡ ታዲያ ይህን ምስቅልቅልነቷን ሳስብ የሙሉቀንን ዘፈን ጆሮ እነሳና የጋሽ ጥላሁን አንዳንድ ነገሮች ትዝ ይለኛል፡
ጋሽ ጥላሁን በአንዳንድ ነገሮቹ አንዳንድ እንደኔይቱ አይነቶቹን አንዳንድ ባህርዮች ይጠቅሳል፣ እንደነገርኳችሁ የኔይቱ እጮኛ ሲያዩአት
ለሰውነቱ ግድ እንደማይለው ፈላስፋ ደራሲ ምናምን አስተኔ ናት፣ የሆነ የጥበብ ውቃቢ ያረፈባት ቆንጆ ሙሁር ትመስላለች ሲቀርቧት
ደግሞ ትዘባርቃለች ለዛም ነው ጋሽ ጥላሁን አንዳንድ ነገሮች በሚለው ዘፈኑ
አንዳንድ ሰው አለ የሚመስል ሊቅ፣
ቀርበው ሲጠይቁት የሚዘባርቅ፣
ያለው፡፡ይህን ሁሉ እያሰብኩና በውስጤ እያቀነቀንኩ
ሳለ ’’ወራጅ ወራጅ፣ ወራጅ ሳይሻገር በናትህ’’ እያለ እኔንም እየረጋገጠ ባጠገቤ አለፈ እኔም ደግሞ ወደ ሌላ ሀሳብና ዘፈን ሳልሻገር
ሰፈሬንም ሳላልፍ እዚህ ላይ ለዛሬ ልረፍ ሀሳቡ ግን አላበቃም ሌላ ቀን በዚሁ ተሸግሮ ነው እሚወርደው……ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment