Tuesday, July 29, 2014

ወይኖና እኔ/

ሰፈራችን ምናብ ሆቴል እሚባል ቀውጢ ሆቴል አለ ፡ ታዲያ ብዙ ጊዜ ጥቂትአመሻሽቼ እገባለሁ እያልኩ እዛው እየነጋብኝ ተቸግሪያለው ፡ እንደውም የሆነ ቀን ከጋለ ጭፈራ ላይ አቋርጨ ሽንት ልደፋ በሩን ገፋ ሳደርግ ለካ ነግቶ ኖሮ አዳሜ ለስራ እየተሯሯጠ ምድረ ወያላ ‹‹ቄራ ሜክሲኮ ፤ ሜክሲኮ ናችሁ?›› ሲል አይኔን ማመን አቅቶኝም ያውቃል፡፡
እንደምታዩት ምናብ ሆቴል ስሙ ይገርማል ፡ እንደ ስሙ ቤቱም ገራሚ ነው እረ፡ ምግቡ ሁሉ (እኔ በልቼ አላቅም እንጂ) ገራሚ ነው አሉ ፡ ስለመጠጡ እንኳን ለኔ ተውት እንደው ሀገራችን ኋላ ቀር በመሆኗ የአመቱ ምርጥ ጠጭ ምናምን ተብሎ አመታዊ ሽልማት የለም እንጂ ቢኖር ኖሮ እኔ ነበርኩ ዋንጫውን በየአመቱ በሁለት እጄ ከፍ እማደርገው ፡ ግን ምን ዋጋ አለው እንደስሙ ምኞቴ ሁሉ ምናብ ሆኖ ቀረ፡፡
ሜሮን ፣ ሜላት ፣ ሄሮን ፣ ሄለን ምናምን እሚባሉ የቅንጦት ስሞች እኛ ሰፈር አይዘወተሩም ፡ ይልቁኑ ባርች ፡ ቀዮ ፡ ወይኖ የተባሉ ተቀፅላ ስሞች ይበረክታሉ ፡ እነዚህ ስሞች ታዲያ አብዝሀኛውን ጊዜ ከስም ከለር እና አኳኋን ጋር ተያይዘው የሚወጡ ናቸው፡፡ እንዳንዴ እንደውም ዝንጀርና አይጦ ሁሉ እሚባሉ ስሞች እሚወጡበት ዘመን አለ እንዳልኳችሁ ይኸም ከመልክ ጋር ተያይዞ የሚወጣ ስም ነው ለምሳሌ ለምን አይጦ እሚባል ስም አወጣችሁ ብላችሁ አትጠይቁም እንጂ ከጠየቃችሁ ልጂቷ አንዳች የሆነ አይጥማ ከለር የተላበሰች ሲሆን ባጭሩ ታዲያ አይጦ እንላታለን ስትቆላመጥ (ድንቄም ቁልምጫ)፡፡
እንደለመድኩት ምናብ ሆቴል ሄጄ ካልተቀመጥኩ እሚያመኝ ሁሉ ስለሚመስለኝ ባይኖረኝ እራሱ ያው በክሬዲትም ቢሆን ፉት ሳልል አልገባም ፡ ከስራ እንደወጣሁ የሆነ ቀን ከሚያካፋው ዝናብ ለመሸሽም ቶሎ ሄጄ አቦል ድራፍት ፉት ለማለትም (ሆ የድራፍትም አቦል አለው እንዴ) እየሮጥኩ ገባሁ ታዲያ ገና ከመግባቴ ዘወር ስል ምን ባይ ጥሩ ነው ? አለም ዘጠኝን ፡፡ አለም ዘጠኝ ማለት ወይኖ ናት ወይኖ ማለት እንደገና ወደ ትክክለኛው መዳረሻ ስም ስናቀና ወይናለም ማለት ነው፡፡ አለም ዘጠኝ እምትላት ታዲያ አርጊቷ አክስቴ ናት ፡ ያ መንገደኛ ገትሮ የሚያስቀረው ፡ ያ የሹፌርን አቅል አስቶ በደንብ እንዳይዘውር የሚያደርገው ፡ ያ በላይዋ ላይ ሲሽከረከር የብቻው ነፍስ ያለው እሚመስለው መቀመጫዋ ነው እንግዲህ አክስቴን አለም ዘጠኝ እንድትላት የገፋፋት ፣ ሁሌም ስታያት ‹‹ አንቺ ወንድሜ ሞልቶልሻል በደህና ቀን ይኸን እቃ ሰጥቶሽ›› ‹‹ አለም ዘጠኝ ሆኖልሻል ምናለብሽ›› ‹‹አለም ዘጠኝ ፡ እረ አለም ዘጠኝ….›› እያለች ነው እምትጠራት፡፡
እና ምናብ ሆቴል ደርሼ እንደተገተርኩ ዘወር ስል ያጋጠመችኝ አለም ዘጠኝ ወይንም ወይኖ ናት ፡ ክው ነው ያልኩት ለምን እዚህ ስገባ አየችኝ ሳይሆን እንዴት እኔን ፈልጋ መጣች ነው ያስደነገጠኝ ‹‹እዚህ ለመግባት እንዲህ ትሮጣለህ ፡ ገርመኸኝ እኮ ነው የተከተልኩህ›› አለችኝ ፡ እኔም ከግርታዬ ለመውጣት ብዬ የሆነ ነገር ቀባጠርኩ ፡ እኔም እንደሚገርምሽ አውቄ እኮ ነው የሮጥኩት ወይኖ አልኳት ፡ ‹‹ተው እንጂ አይተኸኝ ነበር እንዴ ባካባቢው›› እረ አላየሁሽም ያው ምን ሰፈርሽ አይደል እንዴ ከሰፈርሽ አትጠፊም ከጎዳናውም ጭር አትይም ብዬ በመገመት ነው ምናምን ብዬ ቀበጣጠርኩ፡፡
ይበርዳል አይደል ነይ እስቲ ትኩስ ነገር ልልቀቅብሽ ብዬ አጄን ትከሻዋ ላይ ጣል አድርጌ የሆነ ጥግ ላይ ሄደን ተቀመጥን፡፡ ‹‹እሺ እንዴት ነው ተሰየምሽ ጃል?›› አለኝ አስተናጋጁ የምን ልታዘዝህ ፊቱን ወደኔ ጥሎ፡ ‹‹ዛሬ ደሞ አጀብ ብለሽ በዛ ብለሽ ነው የመጣሽው ልበል›› አለ ፡እንዴ እያየ አይደለ እንዴ ምን ልበል ይለኛል ያሰበውን ዝም ብሎ አይልም ምን አይነት ሰው ነው ፡ ደሞኮ ብሎታል በቃ ምኑን ነው ምን ቀረውና ልበል ምናምን ብሎ እሚቀባጥረው አልቀረብህም ፎግረህ ልብህ ውልቅ ብሏል አልኩ በውስጤ፡፡
እሺ ለኔ የተለመደውን አምጣልኝ ከዛ ተናግሬ ሳልጨርስ እራሱ ወዲያው አንገቱን ቀለሰና ‹‹አንቺስ ቆንጆ ምን ይምጣልሽ?›› አላት ‹‹ ወይን ይምጣልኝ›› አለች በሙሉ አፏ ፡ ከዛ ከመቅፅበት አስተናጋጁም ተሰወረ እኔም እጄን ኪሴ ሰደድኩ ፡ የልምድ ጉዳይ ሁኖ እጄን ብቻ በመስደድ ብሩን ሳላወጣ መቁጠር እችላለሁ፡ አስር ብር ፣ አንድ ብር ፣ ሀማሳና መቶውን ሁላ በድምፅ እለያቸዋለሁ ፡ ታዲያ እጄን ሰድጄ ቆጠርኩ አሰይ ተመስገን አልኩ ቢያንስ 580 ብር አለኝ፡፡ ግን እሷ ምን ነካት ፡ እኔ ትኩስ ነገር እንጠጣ ብዬ ነው ያስቀመጥኳት ፡ ዘላ ወይን አምጣልኝ ሆ እውነትም አለም ዘጠኝ አልኩ በውስጤ አክስቴ በምትጠራት ስም፣
እሺ ወይኖ ቀሽት
‹‹እሺ አጅሬው›› አለችኝ ስሜን እንደማታውቀው ፡ አጅሬው ነው እሚሉኝ ሰፈር ውስጥ ታዲያ እኔም ለምጄው አጅሬውን እንደስም ከቆጠርኩት ሰነባበትኩ እንደውም በስሜ ሲጠሩኝ መደንገጥ ጀምሪያለሁ በቃ አጅሬው ተመችቶኛል ፡ ለምን አጅሬው እንዳሉኝ ግን ጠይቄ አላቅም ፡ አንዳንዱ ሁኔታዬንና የምናብ ሆቴል ጀብደኛነቴን አይቶ ነው አጅሬው የሚለኝ አብዝሀኛው ሰው ግን ስሜ እየመሰለው ነው ‹‹ደህና አደርክ አጅሬው ፣ አክስትህስ ደህና ሰነበቱ አጅሬው ፣ ስራ ጥሩ ነው አጅሬው›› ብሎኝ እሚያልፈው፡፡
ወይኑ ከች አለ ፡ ያን አለንጋ ጣቷን በጠርሙሱ አንገት ላይ ያረፈውን እጇን በተመስጦ ሜታዬን እየተጎነጨው ማየት ጀመርኩ ፣ ከኮካ ጋር ቀላቅላ ወይኑን አየሁት ፡ የሷን ፊት አየሁት ፣ ቡቱ የተቀባውን የግርግዳ ቀለም አየሁት ፣ ምን አይነት ወይናማ ቀን ነው አልኩኝ ፣ በምናብ ተሰደድኩ እውነትም ምናብ ሆቴል አልኩ ገና ሁለት ሱስቴ እንኳን ሳልጎነጭ ምሰጣዬ ከቀጠለበት ያ ቀዥቃዣ አስተናጋጅ ዛሬ መቸም ያለወትሮው ተንቀዥቅዧል መጣና ‹‹እ እናቱ መቀመጫ ልጨምርልሽ?›› አላት ፡ ክው ነው ያልኩት ፡ ሊያልቅ የሚችለው ነገር ቢያንስ እምትጎነጨው መጠጥ ነው ፣ ወንበር አያልቅ እንዴት ልጨምር ይላል ብዬ ወደ ታች ወደተቀመጠችበት መቀመጫ አይኔን ወረወሩኩ ፣ ለካ እዛ ቤት ውስጥ ያለው ተስተናጋጅ ሁሉ አይኑ ከገባን ጀምሮ የወይኖ መቀመጫ ላይ ነው የከተመው ፣ ለካ የወይኖም መቀመጫ ያረፈበት የሆቴሉ መንበር አልበቃው ብሎ ዳርና ዳር ተንከርፍፏል ፣ እናም ‹‹ፊት ለፊት ቆሞ ሲከታተል የነበረው የሆቴሉ አስተዳዳሪ ነው የላከኝ›› አለኝ አስተናጋጁ ፣ ለምንድን ነው የላከህ ‹‹በቃ እዛ ሆነው ብታየው እኮ ወንበሩ ያሳዝንሀል በጣም አጨናንቃዋለች ቆኒጂት›› እና ብሎ ቀጠለ ‹‹ሂድ ወንበር ትቀይር ወይ እሱ ይቀፋት ፣ እኛ ወንበሩን እንፈልገዋለን በላቸው ስላለኝ ነው ይቅርታ ›› አለ ጨዋ መሳይ አንገቱን ቁልቁል ቀልሶ……..

…….ክፍል ሁለት….ይቀጥላል 

Tuesday, July 22, 2014

ገጠመኝ

ትዝታ ጋረደው ፣ ትዝታ ጋረደው ምነው የኔን ፍቅር ነው የኛን ፍቅር ብቻ ይሄን ዘፈን እያንጎራጎርኩ ሱሪዬን እፈታታለው ፤ ፓንቴን ዝቅ አደርጋለው ከዛ በቃ ተመስጨ ኩሴን መጣል እንደጀመርኩ ፣ ‹‹ትዝታ ጋረደው ከምትል ፣ ግርግዳው ጋረደው እያልክ አትዘፍንም እንዴ›› አትለኝም ልጂቷ ክው ነው ያልኩት ፡ ምን ማነሽ አልኳት ደንግጨ ፡ ‹‹ማንም ልሁን›› ልጂቷ ከዛኛው ሽንት ቤት ክፍል እያማጠች ወሬዋን ቀጥላለች ፡ ‹‹ብቻ አሁን የጋረደን ግርግዳ እንጂ ትዝታ አይደለም ብዬ ነው አራሙ›› አለችኝ ጭራሽ
እሷም አንደኔ ወጥሯት ኑሮ ታዲያ በየመሀሉ ‹እህ፣ እህ› ታበዛለች በኔ ጎን ያለው የሴቶች ሽንት ቤት ውስጥ ተቀምጣ ፣ ታስቀምጣለች፡፡ በጣም ስላናደደችኝ እንዴ የኔ እህት የት ነው ቆይ የምንትዋወቀው ፣ ደሞስ ምን አገባሽ ፣ ጋሽ ሙሀመድ እኮ ይሄን ዘፈን ሲዘፍን እንዳንቺ አይነቱን ሽንት ቤት ለሽንት ቤት የምትውል ሴት አስቦ አይደለም ፡ የማታ ጀንበርን እያዩ በባህር ዳርቻ ለተዝናኑ፡ በምሽት ጨረቃ ተቃቅፈው ለደመቁ ፡ ማሪንጌ ለደነሱ ፡ ለጥ ባለ ቄጠማ ሳር ላይ ለቦረቁ ነው ትዝታ ጋረደው የተባለው እናቱ አልኩኝ በዝርዝር ተናግሬ ሊወጣልኝ…
‹‹እና አንተ አሁን አዋሳ ወይስ ጣና ሀይቅ ዳር ያለህ መስሎህ ነው ፡ ነው ወይስ ነጭ ሳር ሜዳ ላይ ተንጋለህ የምትዝናና መስሎህ ነው›› ሳልመልስላት ቀጠለች እረ ‹‹ቆይ ጥንብ ሽንት ቤትና መዝናኛ ቦታ እንኳን ለይተህ አታውቅም እንዴ?›› አለችኝ
እሺ ጨረሽ ተናግረሽ አልኳት…..‹‹ባልጨርስስ ምን ታመጣለህ›› እንዴ ይቺ ሴትዮ ማን ነው የላከብኝ ስል ለብቻዬ አሰብኩኝ ፡ ቤት ጭቅጭቅ ፣ መስሪያ ቤቴ ጭቅጭቅ ፣ ሰው ሽንት ቤት እንኳን እራሱን አያዳምጥም ፣ ፈታ አይልም ስል ደሞ ለካ ቀስ ያልኩ መስሎኝ ሰምታኝ ነበረ ‹‹ ስማ ሽንት ቤቱንስ ማን ያንተ አረገው ቆይ?›› ንድድ አለኝ ፡ ፈሴ ሁሉ በቃ ቁርጥ ቁርጥ አለ
ሴትዮ እኔ ነግሬሻለው እኔ ተይኝ ልራበ……..አንቺም አርፈሽ አርተ…….ውጭ  በቃ ምን አለፋቹ ክፉ ባልና ሚስት መሰልን….
‹‹ኡኡቴ የኛ የተረበሸ ሰው አልቀረብህም ባክህ አሀሀሀሀሀሀ፡ደሞ ምን በልተህ ነው እንዲህ እንደጀነሬተር እምትንደቀደቀው ፡ አሁን ውጭ ሲያዩህ ሰው ትመስላለህ›› ጉድ ፈላ እምታቀኝ ሰው ናት ማለት ነው ፤ ሀሳብ ያዘኝ ደሞስ አጩሆ እሚፈሳ ሰው ሰው አይደለም እንዴ ፤ ሰው ትመስላለህ ያለችኝ ፡ እሷ እኮ ይሄኔ ከውሀ የቀጠነ ፈሳሽ ይሆናል እምትፀዳዳው ስል ተፅናናው ነገር ግን እንደጀነሬተር ትንደቀደቃለህ ያለችኝ ነቆራ አልወጣልኝም ፡ ልያትና ይለይልኝ አንቄ ነው እምጥላት ብዬ በደም ፍላት ስወጣ እሷም ወጣች ፡፡
አቤት ከኔ እርሳቸው አፈሩ ፣ ከኔ እርሳቸው አነሱ ፣ የተከበሩ የባላንባራስ ባለቤት ወ/ሮ አበበች አከራዬ ናቸው ፡ በጣም የገረመኝ በማን አፍ ተውሰው ሲሰድብኝና ስዘልፉኝ እንደነበር ነው ፣ ለካ ብዙ ሰው ማንነት ውስጥ ብዙ አይነት ማንነት አለ ፣ አውቀው ነው ለካ እንደትልቅ ወ/ሮ በግድ በትልቅ ሴት ድምፅ ነጋ ጠባ ሰላም እሚሉኝ ፣ ድምፃቸው የአንዲት ዘላ ያልጨረሰች ኮረዳ ነበር እኮ የሚመስለው፣ ልክ ስንተያይ ታዲያ ባንዴ እንደ ዱሮው ቅይር ብለው ‹‹ውይ ውይ ውይ አንተ ነህ እንዴ ልጄ ፣ እኔን እንዴት ቀለልኩ ልጄ ያ የመናጢ ልጅ አለ ›› ብለው የሆነ ባለጌ ያሉትን ሰው ስም ጠሩልኝ….

እኔ ግን አፈርኩባቸው እኔም አብሬ ብቀልም ቅሉ ከሳቸው ግን ከአንድ ባላንባራስ ሰፈር ውስጥ አንቱ የተባሉ ሰው ሚስት ድምፅ ቀይሮ ሽንት ቤት እየተቀጣጠሩ ሲሰዳደቡ መዋል አዲስ ያልታየ ገመናችን ነው መሰለኝ ፣ ሆ ደሞኮ የሰደቡኝ ስድብ ቆማጣ ያሮጣል በስተርጅና አራዳ ናቸው፣ አይጣልባቹ አንዳንድ ቀን………ባልተመቸ ስፍራ ከአከራይ ጋር ይጣሏል፡፡

እውቀት


ፒያጌት የተባለች ሳይኮሎጂስት፡ እውቀት ሁሉም ጋር ይገኛል ትለናለች ማለትም ህፃናትም ጋር አዋቂዎችም ጋር ነገር ግን ልዩነቱ የመጠን፣ የጥልቀት እና የብዛት ነው ትላለች፡፡ እድሜና ጊዜ አያስተምርም አይባልም ያስተምራል ግን ስንቶቻችን አይናችንን ገልጠን ጆሯችንን ከፍተን እጃችንን ዘርግተን አፍንጫችንን አፈንጭተን፣ ምላሳችንን አውጥተን እውቀት እንቀምሳለን? ነው ጥያቄው በተለይ ደግሞ በአዋቂዎች ስም ተጠርተን በዛ ደረጃ የምንገኝ ሰዎች በዚያ ዘርፍ መገኘት ብቻውን እውቀት ይመስል ህፃናትን እንወቅሳለን በሌሎች ከኛ በእድሜ ባነሱ ሰዎች እናፌዛለን፡፡ አንድ የአራት አመት ህፃን ልጅ አባቱን ሊያውቅ ይችላል እናቱን በደንብ ይለያል ነገር ግን አያቶቹን ቅድመ አያቶቹንና ቅማት ምዝላቶቹን ላያውቅ ይችላል ይህ የሚያመለክተው የልጁን የእውቀት ጥልቀት እጥረትና ማነስ ነው እንጂ የልጁን አለማወቅ አይደለም ምክኒያቱም ቢያንስ ከቤተሰቡቹ የመጀመሪያዎቹንና ዋነኞቹን አውቋልና፡፡ ወላጆቹ ግና ከነ ዘር ማንዘራቸው አበቃቀል ከነ አመጣጣቸውና አስተዳደጋቸው ያውቃሉ ይህም በአንድ ቀን የመጣ ታምር አይደለም ሲጠይቁ ሲፈትሹ በህይወት ኑረው ያወቁት ነው፡፡ ህፃን ትልቁን ሰው እሚበልጥበት ብዙ ነገር አለው እንዲሁም ትልቁ ህፃኑን እሚበልጥበት ብዙ ዘርፍ አለው፡፡ ለምሳሌ ህፃን ልጅ ቂም አይዝም እሚናገረውም በቀጥታ ነው እሚናገረውን ነው እሚሆነው እንዲሁም የዋህ ነው ነገር ግን ትልቁ ሰው ቂም ይይዛል ሁሌም ፍልስፍና አይሉት ቅኔ አዙሮ ማሰብ ይወዳል ቀጥተኛ ሀሳብም የለው የዋህነትም ይጎድለዋል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የሁለቱ የህይወት ጎራ ሁል ጊዜም የህፃኑ ባህሪ ለራሱ አይጠቅመውም ሁልጊዜም አይጎዳውም፣ በተመሳሳይ ለትልቁም ሰው እንዲሁ ይህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ያለን የህይወት ወይንም የነገሮች እውቀት መጠንና ጥልቀት እንጂ ፍፁም አለማወቅ አይደለም እንደውም ፕላቶ እንደሚለው የሰው ልጅ በተፈጥሮ አላዋቂ አይደለም አብሮት የተወለደ አንዳች ማወቂያና እውቀት አለው እንጂ፡፡

Monday, July 21, 2014

አመሌ


……….
አመሌ…..


ነይ በሳቅሽ ምጭ
ስቀሽ ተገለጭ
ሳቄ ንስሀ ናት
የመሆን ፍስሀ
በደሌን ክፋቴን እውነቴን ቅዠቴን
ምፀቴን ቅናቴን ደስታና ድብርቴን
የመንገር አምሀ
….
ደሞም ይሄ ሳቄ
በጥርሶችሽ ሰበብ የመሳብ መግነጢስ
እንዳልታየ አውሊያ እንዳይነኩት መንፈስ
መላ ጉንጬን መሀል ድዴን ሲያተራምስ
ሲሄድ ሲንከላወስ
ሳቅ ምግብ ነው ለኔ ሰርክ የማላምጠው
አኝኬ እምውጠው እምሰለጥቀው
ዛዲያ
አኝኬ ስውጥሽ ከአንጀቴ ስዶልሽ
መንፈስ ታድሻለሽ እውነት ትነግሪያለሽ
ደስታ ትፈጥሪያለሽ
ስቅ ስቅ እያስባልሽ
ዳግም ታስቂያለሽ
…….
……
ሳቄ ወግ ነው ለኔ
የሁንኩትን ሁሉ ላንቺ ማወጋበት
እምታዘብበት እምመሰጥበት
እምታደምበት እምደብትበት
እናም መሳቅ ነው አመሌ
ካንቺ መጣባቴ አንቺን መታደሌ፡፡

Friday, July 18, 2014

የክብር ማዕረግ

የክብር ማዕረግ
……….

ለኢኮኖሚስት ገብረህይወት ባይከዳኝ ፣ ለአርቲስት (ፋዘር) ተስፋየ አበበ ፣ ለድምፃዊት አስቴር አወቀ እና ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለኛ የሰሩልን የኛን ሰዎች ከዚህም በላይ ብናከብራቸው ምንኛ ደስ ባለኝ ፣ በተለይ ደግሞ በህይወት እያሉ ይህን ክብር መስጠት ባለሙያዎቹ አገራቸውን፣ ዜጋቸውን እና ሙያቸውን የበለጠ እንዲወዱ እና በሰሩት መልካም ስራ እንዲኮሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ትንሽ የክብር ዶክትሬቱ አሰጣጥ ላይ የሆነ ነገር ብል ደስ ይለኛል፡፡
ለምንድን ነው አስቴርን ጎንደር ዩንቨርስቲ የሰጣት?
ለምንድን ነው ገ/ህይወት ባይከዳኝን መቀሌ ዩንቨርስቲ የሰጠው?
ለምንድን ነው ለጥሩነሽ ዲባባ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሰጠው?
አስቴር የዘፈነችው ስለ እያንዳንዳችን ፍቅር ነው ፣ ባህል ነው ፣ ሀሳብ ነው ፣ ለጎንደር የዘፈነችው ዘፈን አለ ፣ በጉራግኛ የተጫወተችው ዘፈን አለ ብቻ ምን አለፋቹ አስቴር በሙያዋ አንቱ የተባለች ምርጥ ድምጻዊት ናት ታዲያ ጎንደር ስለተወለደች እና ጎንደሬ ስለሆነች ነው ጎንደር የሚሰጣት? ቆይ እኔ እምለው የያሬድ ሙዚቃ ት.ቤት ምንድን ነው ስራው? የሀገሪቱ ታላቅና አንጋፋ የዚህ ዘርፍ ባለቤት ነው ስለዚህም በኔ እምነት እያንዳንዱ  ስራ ሲሰራ በዘርፍ ሲሆን ደስ ይላል፣ አስቴር በያሬድ ት/ቤት ላታልፍ ትችላለች ነገር ግን ይህ ሀገራዊ የሙዚቃ ተቋም ሀገራዊ ሙዚቀኞችን ቢሸልም እሚያምርበት እሱ ነው፡ ያሬድ ት/ቤት ዶክትሬት መስጠት የለበትም ቢባል እንኳን የሀገሪቱ ትልቁና አንጋፋው የመጀመሪያው ዩንቨርስቲ አ.አ.ዩ ነው መስጠት ያለበት ባይ ነኝ ዘሎ እንደው ሁሉን በክልል ማሰብ ቢቀርብን መልካም ነው ጎበዝ፡፡
የገ/ህይወት ባይከዳኝም ጉዳይ እንዲሁ ነው መሆን ያለበትትትትት…..ለምንድን ነው በግድ በክልል እምንጠርፋቸው ? እሳቸው ምርጥ የኢትዮጲያ አይደሉም የአፍሪካ ኢኮኖሚስት ነበሩ ፣ ማንም ፈረንጅ የሚቀናባቸው ጭንቅላት የነበራቸው ሰው ነበሩ ፣ እሳቸው ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ ናቸው እሳቸውን የመሰለ ሰው ዶክትሬት ቢደራረብ ልዩነት የለዉም እንጂ ሁሉም ዩንቨርስቲ አንድ አንድ ዶክትሬት ቢሰጧቸውም አንቀየምም ነገር የሀገሪቱን ምርጥ እኮኖሚስት የሀገሪቱ አንጋፋውና ትልቁ ዩንቨርስቲ አሁንም አ.አ.ዩ ነው መስጠት ያለበት መቀሌ ከፈለገ ሌላ ማዕረግ ይስጣቸው እንጂ መጀመሪያ በሀገር ደረጃ እናስብ ሮጠን በትውልድና በሀረግ በክልል ምናምን እነሱ እኮ ሲሰሩ እውቀታቸውን ለመቀሌ ፣ ለጎንደር ለባሌ እያሉ አልከፈሉም እንደ ኢትዮጲያዊነት ነው የኖሩት እኛም ታዲያ እንደ ኢትዮጲያዊነት ልንሸልማቸው ይገባል፡፡
ሌላው እና በጣም የገረመኝ ነገር ለጥሩነሽ ዲባባ በመጀመሪያ እራሱ ዶክትሬት መሰጠቱ ትንሽ የቸኮልን መስሎኛል ፣ እንዲህ ስል እምትበሳጩ ትኖራላቹ እኔ ምናገባኝ እኔ የኔን ነው እምናገረው እናንተ የናንተ ስላላችሁ የናንተንም አውጉ፡፡ ገና ሀያ ቤት ላለች ወጣት ከአቅሟ በላይ ሰርታ ብታኮራንም ቅሉ ትንሽ መቆየት የነበረብን ይመስለኛል ፣ ዶክትሬት ካልሰጠናት ለሌላ አገር ትሮጣለች ተብሎ ተፈርቶ እንደሆነ አላቅም፡፡ ቢያንስ ሀይሌ ዶክትሬቱን በሰጠንበት እድሜ ፣ ቢያንስ ለደራርቱ ቱሉ ዶክትሬት በሰጠንበት እድሜ እስክትደርስ ብንጠብቃት መልካም ነበር ፡፡

በመሰረቱ እኔ እሚገባኝ እስከዛሬ ሰዎች ትልቅ ከሆኑና አቅማቸው በመዳከም ሁኔታ ላይ ሲገኝ ነው ዶክትሩት የሚሰጠው እንደዛ ስል ግን ለእነ ሀዲስ አለማየሁ እና ከበደ ሚካኤል የተሰጠው አይነት በጣም ከረፈደ አይነቱን እየደከፍኩኝ አይደለም፡፡ ጥሩዬ ገና ልጅ ናት ቀስ ብሎ ሊደርስ ይችላል ባይ ነኝ በተጨማሪም ተስፋ እያደረገችም ብዙ እንድትሰራ ያስችላት ነበር ትን ቢዘገይ ምንም እንኳን አሁንም እንደማትሰንፍ ቢገባኝም፡፡ሌላው ጉዳይ አሁንም ዘርፉን የወከለ ኢትዮጲያዊ ባለቤትነት ጉዳይ ነው ፡ ለመሆኑ ቆይ ሀገሪቱ ውስጥ የአትሌቲክስ ት/ቤት ወይንም የት.ምርት ክፍል የለም እንዴ? በአትሌት ዘርፍ እርግጠኛ ባልሆንም ኮተቤ ያለው ይመስለኛል ካለ ታዲያ ምን አገባውና ነው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዶክትሬት የሚሰጠው? ነው ወይስ እሷ አዲስ አበባ ስላደገች ይሄም በክልል መሆኑ ነው? በክልልማ ስለሆነ ነው ለደራርቱም ጂማ ዩንቨርስቲ የሰጣት እንጂ ሁሉስ አንድ ዘርፍ አልነበሩምን? እኔ እንዲህ ባይሆን ጥሩ ነው ባይ ነኝ ኢትዮጲያኖችን ስናከብር እንደ እትዮጲያ ቢሆን ደስ ይለኛል….

Saturday, July 12, 2014

ለፀጋዬ አጭር ደብዳቤ

በካሌብ (ስንታየሁ) አለማየሁ


ለፀጋዬ አጭር ደብዳቤ
……………

አዎን አንተ ላንተ ኑረህ አታውቅም
የኛን ኑሮ ስትከረክም
የኛን እንክርዳድ ስታርም
የኛን አቃቅማ እሾህ ስትነቅል
ዝንጉ ነበርህ ለራስህ ውል
………
ታዲያ ምን ያደርጋል አባብዬ
ወዲህ የኛ ትንግርት ሌላ ነው
የኛ ጀብዳችን ልዩ ነው
ለሞቱልን መኖር አናቅ
ከጥበብ የተለየን
ከማየት የተጋረድን
ለማከበር የተፋፈርን
ነውር የማናውቅ ነውረኞች ነን
………………..
እና አባብዬ ልክ ነህ
ያንተ ውል ከቶ በእውንህ
በቁም ሳለህ በነፍስህ
ያስታውቅ ነበር ክታብህ
አንተን ዘንግተህ ለኛ
ሁሉን ኑሮ መኖርህ
ሁሉን ቅኔ መቃኘተህ
ሁሉን እይታ ማየትህ
ደፋር ነበር ብእርህ
ከሰይፍ አፋፍ የቆመ
እውነት ነበር ምናብህ
ለትውልድ ድህነት የታደመ
ንስር ነበሩ አይኖችህ
አጥንት ፈልቅቀው የሚያዩ
ግማድ ሀረጉን ሚተነብዩ
ደምን ከደም የሚለዩ
ፀጋዬ አንተ እንደስምህ ፀጋ ነበርክ
የህይወታችን አክሊል የብዕር ግርማ የተባልክ
………..
ፀጋዬ እኔ አንተን አይደለሁ
በምን ስንኝ በምን ቅኔ
አንተን ምን ብዬ እገልፃለሁ
ብቻ አልኩ ለማለት ብዬ
ስራህ ትዝታህ ከነፍሴ ከቁም አካሌ ባይጠፋ
ሌላውም ዝም እንዳይልህ ስምህ ከልቡ እንዳይጠፋ
ይቺን ስንኝ ሰደርኩልህ
ይድረስ ላንተ አባብዬ ባለህበት በሌላ አለም
መቸም ነፍስህ በገነት ናት ሌላ ስፍራ ለሷ የለም
ይኸው አንተን ከሸኘን በስቲያ
ማን ይናገርልን
ማን ባይናችን ይይልን
ማንስ በጆሯችን ይስማ
ማን በጣታችን ይፃፍልን
አንተ ነበርክ ፀግሽዬ
አመትባሉን ልቅሶውን
አብዮቱን ጥምቀቱን
ግርግሩን ጭርታውን
ክርክሩን ውይይቱን
ፍቅርና ጥላቻውን
እኛን ሆነህ የኖርክልን
ታዲያን ዛሬ ብቻችንን የብዕር ዋግምት ሲቆጋን
ማንም ሀዬ አላለን
አንተም አትመለስም
መንፈስክም ከትውልዱ የለም
ብርታትክም ከኛ ዘንድ የለም
እና ስማኝ አባቴ
ፀግሽ ልንገርህ ካንጀቴ
ዛሬ እኛ ብዙ ሺ እጦት
ብሶት ሆይታ አለብን
ከዕጦቱ ሁሉ እጦት ግን
አንተን እጦት ነው የባሰን
ጭንቃችንን ከጭንቀቱ
ምጣችንን ከምጡ
ቀላቅሎ የሚኖርልን
………….
እናም ይድረስ ላንተ ባለህበት
የእውነት ዛሬም ከልብህ
ከውስጥ ከአንጀት ከደምህ
ትወደን እንደሆነ
መንፈስክን በደህና መንፈስ ጠቅልለህ ላክልነ
ብርታትክን በደህና ብርታት አጅለህ ስደድልነ
ድፍረትክን በደህና ድፍረት ጠምጥመህ አኑርልነ

እውነትክን በሙሉ ሚስጥር ጥበቡን ሹክ በለነ፡፡

Tuesday, July 1, 2014

ምስል


ፎቶው ይናገራል?


ወዳጄ ምን ተማርክ ወዳጄ ምን ተማርሽ
ከፊት ከገፃቸው
ከአቀማመጣቸው
ከአሰዳደራቸው
ከአተያያቸው
ከረጋ ፊታቸው
ከጭምት ደማቸው
ከላይ ከልብሳቸው
ከቆብ ካቦርታቸው
ከሸሚዝ ሱፋቸው
ከጦር ከጋሻቸው
ምን ታየህ ወዳጄ
ምን ተማርሽ ወዳጄ
አይንህ ምን ነገረህ
ምን አለምክ ወዳጄ?
በትረ ስልጣኑ ከፍታው ነው የታየህ?
እውነት መሀል መቆም ክብደቱ ነው የታየህ?
አይንህ ምን ነገረህ?
ነው ወይስ ዝም ብሎ የቆመ ስዕል ገፅ
ፎቶው ነው የታየህ?
ንገረኝ ወዳጄ ንገሪኝ አይንሽን፣
ጥልቅ ምልከታህን ረቂቅ እውነትሽን፣
ፎቶው ይናገራል የሚል ብሂልሽን፡፡