Friday, October 4, 2013

ኦ ያያያያያ….




ኦ ያያያያያ….                   
                               (በካሌብ አለማየሁ)
                                                                             
ይህን ኦ ያያ የሚል ቋንቋ መቸም ስፖርት ለሚወድ ሰው ፣ከስፖርትም እግር ኳስ ለሚወድ ሰው፣ ፋና ኤፍ ኤምን ለሚጫን ሰው አዲስ አይደለም፣ እኔም ይህች ኳስ ለሚሏት ፣ ለ 1፡30 ሰአት 22 ሰዎች በእግራቸው ለሚለጓት ክብ ግዑዝ ነገር አፍቃሪ ነኝ፡፡ ኳስ ለኔ በጣም እምትገርም  ሰው  ሰራሽ ፍጥረት ናት፡፡ እርሷ በየሳምንቱ በትንሹ ከ 400 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በዙሪያዋ የሚጮሁላት ናት፣ በስንት ሺ ዳኞች እንክብካቤ የምተትታጀብ ናት፣ በ ስንት ሺዎች በሚቆጠሩ ሰላም አስከባሪዎች የምትከበብ ናት፣የተለያየ ህብረ ቀለም ባለው ውብ ፣ሸንቃጣ ቲሸርትና ቁምጣ፣ በለበሱ ሰዎች እግር መሀል የምትውል ናት፣በእርሷ ስምና  ስለ እርሷ ስንት ሺህ ክበቦችና ክለቦች የተቋቋሙላት ናት፣ ስለ እርሷም ሀገሮች ባንዲራ አንግተው ለግጥሚያ ጎጥ የለዩባት ናት፣ በእርሷ ስም እልፎች እንጀራቸውን አንጉተዋል፣ የየእለት ጉርሳቸውን አበጅተዋል፣ በእርሷ ስም  ከቀዬ ከሰፈራቸው ስንቶች ተነጥለዋል፣እሷን በማየት  ስንቶች ደስታቸውን በየሳምንቱ አድሰዋል፣ ስንቶች በስሟ በደስታ ሲቃ አንብተዋል፣ ስንቶች ስንኝ ቋጥረው ፣ ግጥም ፅፈው ዘምረዋል፤ እናም ኳስ ማለት እያባረሩ፣እያጥመነመኑ፣እየደበደቡ ፣ ከወዲያ ወዲህ እየለጉ እየቀጠቀጡ ነገር ግን ከልብ የሚወዷት አስደናቂ ሰው ሰራሽ ፍጡር ናት፡፡ ለነገሩ ወትሮም የሰው ልጅ አውቆ የሞተለትን እሺ ብሎ እሚሸነፍለትን ነው የሚወደው፣ ኳሷም ወዲያ ሲመቷት ዝም፣ወዲህ ሲመቷት ዝም፣ከጎል ሲከቷትም ዝም እምትል ፍጥረት ናት፡፡ ያለ ምርጫ በተፈጥሮዋ ይህን ያክል ገደብ የለሽ ስልጣን ተሰጥቷታል፣ ገደብ የለሽ የሰው ፍቅር አላት፣አለምን ባንድ ላይ ያናገረች የአለም ቋንቋ ሆናለች፡፡ እና ታዲያ ለምን ኦ ያያያያያ አይባልላት፣ ኦያያ ሲያንሳት እንጂ፣ መሰለ መንግስቱ የህዝብ እሷን መውደድ አይቶ " እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ" ሲል ጀመረ፡፡ ለማናያት በምናብ እየሳልን፣ ድቡልቡል ነገር አልመን በደስታ እንድንድቦለቦል አደረገን፡፡ በደስታ መድቦልቦል እኮ አስቡት እስቲ ታላቅ ነገር እኮ ነው፡፡ ድቦልቦል ማለት የአንድ ነገር በተደጋጋሚ ጊዜ መጥመልመል ነው፣በተደጋጋሚ ጊዜ መጠምጠም ነው ፣ እና ታዲያ ድብልቡልዬ ኳስም እኛን በደስታ ከጠመጠመችን ለምን አንወዳት! ኦ ያያ አንልላት፡፡
ባሁኑ ሰአት አገራችንን ኢትዮጲያን ጨምሮ በምእራብና በሰሜን አፍሪካ፣በመካከለኛው ምስራቅና በአረብ አገሮች ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲሁም በተለያዩ ሀገሮች ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ይስተዋላሉ፣ የኢኮኖሚ ውጣ ውረዶች ይታያሉ፣ በዚህም ምክኒያት ሰዎች ይበሳጫሉ፣ ይነጫነጫሉ፣ በፖለቲካውም ምክኒያት ሰዎች ይከፋፈላሉ፣ አንድነታቸውን ይሸረሽራሉ፣ ይሁን እንጂ ይሄ ሁሉ ባለበት ትርኪ ምርኪ አለም ፣ የሰው ልጅ ኳስ እሚባል ነገር በመፍጠሩ በእርሷ ደስታውን ይመልሳል፣ በእርሷ ያጣውን የመቀላቀልና የአንድነት መንፈስ ያድሳል፣በእርሷ ብሄራዊ ስሜቱን ይመልሳል፣ህዝብ ጥቅልል ብሎ እንደ ኳሷ በአንድ ስሜት በአንድነት ይድቦለቦላል፡፡ በዚህች በኳሷ ስር ያየሁት እይታ ይህ ነው፣ የሰማሁትም ደስታ ይበል ነው፣የጨበጥኩት አንድነት የሚታይ ነው፡፡ አለዚያማ እኮ ሌላ ሌላውን ባንነካው ነው እሚሻለው አይደለ እንዴ!? አንድ ጓደኛዬ ስለ ስፖርት ዜናዎች በምሬት አወራልኝ፣ "ነጋ ጠባ ስፖርት፣ስፖርት፣ስፖርት፣ኤፍ ኤሞቹ ሁሉ ስለ ኳስ፣ኳስ ምናችን ነው ?" ሲል አፈጠጠብኝ፡፡ ነገር ግን ጓደኛዬ ለጠየቀኝ ጥያቄ ከላይ ስለ ኳስ የገለፅኩትን ሀሳብ አስረዳሁት፡፡ የስፖርት ዜናዎች መብዛት በጣም ባያስደስተኝም ከንቱ አይጨበጤ፣ ላም አለኝ በሰማይ አይነት፣እኔ እማላውቀው የልማት ዜና ጆሮዬን ከሚያደማው፣ አይኔ አይቶ የሚፈርደው ኳስ ይሻለኛል፡፡ በኛ ሀገር እንዳልሆነ ሁኖ ተተረጎመ እንጂ ሚዲያ ማለት የህዝብ አፍ፣አይንና ጆሮ ነው፣ለነገሩ ዝም ብዬ ልፋ ቢለኝ እንጂ ለካ እንዲህ እሚሆነው መንግስት እራሱ ህዝብ ሲሆን ነው፣ህዝብ መንግስት ባልሆነበት አገር ሚዲያም የህዝብ አፍ ነው ብል ባሸባሪነት መቀጣት ሲያንሰኝ ነው ሆ!፡፡ እና የኛ ሀገር ቆፍጣና ሚዲያዎች ስለምን እና ስለማን አገር እንደሚያወሩ አይገባንም ብቻ ሌላ ኢትዮጲያ በህሊናቸው ሲስሉ ያድሩና በጠዋት ያንባርቁብናል፣ብልጥ የሆነና እንደኔ ኳስ እሚወድ ቶሎ ኤፍ ኤሟን ወደ ስፖርት ይቀይራታል፣ካልሆነም ሬዲዎንዋን ዘግቶ እራሱን ያዳምጣል፡፡ እራስን ማዳመጥ እራሱ ቁዘማ ተብሎ በሚጠራበት ሀገር እሱም ለነገሩ ይከብዳል! ብቻ በቃ ሌላ እርሱ ያሰኘውን ያደርጋል፡፡      

No comments:

Post a Comment