Friday, October 4, 2013

መያያዝና በልማት ጎዳና መንከርፈፍ



መያያዝና በልማት ጎዳና መንከርፈፍ                      
                                                         በካሌብ  አለማየሁ

ቆይ እዚህ አገር ስንት አይነት ጎዳና ነው ያለው? እኔ እስከማቀው የከብትና የእግረኛ ሰው ጎዳና፣ የመኪና ጎዳና እና የማያልቀው ያላለቀው የባቡር ጎዳናን ነው እስካሁን የማቀው፡፡ የልማት ጎዳና ደግሞ የቱ ነው? እሱንም በቻይና መንግስት ስፖንሰርነት ነው እምናሰራው? ነው ወይስ ሌላ እኔ ያላወኩት፣መንግስት የሰራው ጎዳና አለ? አስቡት እስቲ ለያውም እጅ ለእጅ ተያይዘን እምንሄድበት ጎዳና እኮ ነው አለ የተባለው! ሆሆ እንኳን ተያይዘንና ተቀጣጥለን ይቅርና ለብቻችን እምንሄድበት ጎዳና በጠፋበት ጊዜ ይሄ ደግሞ "እጅ ለእጅ ተያይዘን በልማት ጎዳና አንድ ላይ እንጓዛለን" እሚሉት በየት ነው!
ይሄ ሁሉ ጥያቄ የአያቴ ነው ፣ አዲስ አበባን ከተመለከታት በኋላ የተናገራት ትዝብት ናት፡፡ ዕረ እንደሱ ሲባል እኮ አያቴ ፣የእውነት መሬት ላይ የምናየው ጎዳና ማለት አይደለም፣ ይሄ የልማት ጎዳና ማለት በአይን የማይታይ፣ የማይደሰስ የማይጨበጥ፣ ብኩን አይጨብጡት አይነት ሲሳይ ነው አልኩት፡፡ሰማህ ወይ! ብሎ ቀጠለ…..ይቺ ሰማህ ወይ እሚላት ቃል ልክ እንደወሬ መጀመሪያም፣ እንደ አዝማችም እሚጠቀምባት ናት፡፡ እህ ብዬ ጆሮዬን ሰጠሁት እንደልማዴ፡፡
"ሰማህ ወይ፣ አይ አንተ፣ እዚህ አገር ምን እሚታይ ልማት አለ ወትሮስ፣ የማይታይ ልማት ደግሞ እንዳላችሁት የማይታይ ጎዳና ነው እሚኖረው እና እንዳልከው ጎዳናው ባይታይ አይገርመኝም " አለ በረጅሙ ተንፍሶና አንገቱን አቀርቅሮ፡፡አያቴ አሁን እኮ እኔና አንተ ነን እንጂ እዚህ ቁጭ ብለን እምንደሰኩረው፣ ሰው እኮ በዚሁ በማይታየው የልማት ጎዳና እየተምዘገዘገ ነው! አልኩት፡፡
" እና በል እንጂ አንተ….. እንዴት ነው ሰው በማያውቀውና በማይታየው ጎዳና አብሮ አሚምዘገዘገው? " ሲል እንደገና ሞገተኝ ….ያው እንግዲህ አብሮ መደናበሩን ሰው ለምዶት ይሆናላ አያቴ፡፡
"አይይ….በደንባራ መንግስት ላይ ደንበራ ህዝብ ተጨምሮ እንዴት ያል ዘመን ነው ጎበዝ? ዕረ ፈጣሪ አንድ በል ግድ የለህም ተው?"
"ቆይ እኔ እምለው ፣ይኸ በልማት ጎዳና መሄድ ማለት ስኳሩ፣ነዳጁ፣ዳቦውና ዘይቱ ጠፍቶ ተሰልፍን ስንውል ነው ማለት ነው ?" ዕረ እንደሱ አይደለም እባክህ አያቴ……"እህ እንግዲያ እንዴት ነው ፣ እስካሁን መቸም እጅ ለእጅ መያያዝ አይደለም ተቃቅፈን የዋልንበት ጎዳና ቢኖር እነዚህኑ ነገሮች ፍለጋ ስንሰለፍ ነው" አለኝ፡፡
እኔ…ያኔ እኮ ታዲያ ተሰለፍክ እንጂ መች ተራመድክ?
እሱ…ለነዚህ ነገሮች መሰለፍ ሳናቆም እንዴት ነው ልማቱ ነው እምልህ? የኔ ልጅ፣ወዴት ወዴት ወግ ይቀይራል
እኔ…እህ ምን ችግር አለው አያቴ ደግሞ ፣ያው እየተሰለፍን ጎን ለጎን እናለማለን
እሱ….እኛው ተሰላፊ ፣እኛው አልሚ ማለት ነው?
እኔ….እና ማን ይሰለፍልህ?
እሱ…." ካህያ ጋር የዋለች ጊደር ፈስ ተስተምራ ትመጣለች"  አሉ፡፡ወትሮስ ከነሱ ጋር ውለህ ሌላ ምን አንደበት አለህ፣ አንተም እንደኔ እኩል እየተቸገርክ ፣ጭራሽ እኔኑ ትሞግተኝ ገባ…እ…
" አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል አሉ" ግድ የለም ቀን ይወጣል፡፡
እኔ…..አሉ እያልክ እምትተርተው ለምንድን ነው? ካልክ እራስህ በል ማለት የፈለከውን፣ማን እንዳለው እንኳን እማታቀውን ተረት ለምን ትተርታለህ አባባ?
እያልን እየተወያየን ወይም እየተጨቃጨቅን ሳለ እንደሱ ነቆራና ሽምጥ እሚወዱ አንዲት ጎረቤት አሮጊታችን መጡ፡፡
ከነገ ወዲያ የባንዲራ ቀን ነው፡ እትዬ ብርጣሉ አልኳቸው፡፡
እትዬ ብርጣሉ…እናሳ ምን ላርግ ደግሞ? ሆሆ አንተ ልጅ አንደበትህ ካቢኔኛ ሆነሳ እንዴት ነው ነገሩ?
እኔ…..አይ ባንዲራ ይዘው ሰልፍ አይወጡም ወይ ብዬ ነው?
እትዬ ብርጣሉ…  እህ እንዴት ማለት አበል አለው እንዴ? ታለው መቸስ እ.. ምን አደርጋለው ደግ እንዳልኸው ይሁን
እትዬ ብርጣሉ…..እኔ እምለው ባለፈው አመት እንዲሁ በማይረባ ሀምሳ ብር አበል አስወጥታችሁን ስታበቁ አንድ ፅሁፍ በጄ ይዤ ነበር የዋልሁት….ጥፎሹ ምን ይላል ሃልከኝ
ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን
እሚል ነበረ፡፡ አዲያ እንደው አሁን ማን ይሙተ እስቲ፣ ድህነት ነው ፣እድገት ታሪክ የሆነው?
በልማት ጎዳና እንሮጣለን! ትላላችሁ ወገኞች፣ ይኸ በልማት ጎዳና መንከርፈፍ ነው እንጂ ምን መሮጥ ነው፡፡
…………….
እንዲህ አይነት ወግ ከጣማችሁ እስቲ እቀጥላለሁ…..ካልሆነ እንዲህ አይነት ወግ ዘለን ሌላ ማውጋት ይቻላል፣አስተያየት ስጡበት፡፡

No comments:

Post a Comment