Thursday, December 12, 2013

ስምና ሁናቴ
…………….
በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

ስም ያው ብዙ ጊዜ መጠሪያ ነው ፣ አንዳንዶቹ ወላጆች ከሁኔታዎች ጋር እያመሳሰሉ ያወጣሉ ፣ አንዳንዶቹ አፋቸው ላይ የመጣውን ደስ ያላቸውን ስያሜ ይሰጡበታል፡፡ በእኛ ሀገር በተለይ አፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ በሆነበት አካባቢ ስሞቻችን አንዳንድ ግዜ ከአባት ስም ጋር ተገጣጥሞ ትርጉም እንዲሰጥ ፣ እንዲገጥም ፣ መልክት እንዲያስተላልፍ ፣ አንዳንድ ጊዜ ደሞ ተረት መተረቻም ቅኔ መቀኛም ያደርጉታል፡፡ 
ለምሳሌ እኛ ሰፈር የነበረ አቶ አወቀ የሚባል ሰውዬ ፣ የልጆቹን ስም ከሱ ስም ጋር እንዲገጥም አድርጎነው ያወጣሁ፣ መቅደም አወቀ፣ መስጠት አወቀ፣ ወ/ሪት ማታለል አወቀ፣ መሳቅ አወቀ፣ እና ወላጆች አንዳንዴ ሳስበው ለነሱ ከነሱ ጋር የሚሄድ ስም ይሁን እንጂ ምንም አይነት ቃል ይሁን በቃ ዝም ብለው ይለጥፉብናል ፣ በቃ ‹‹ምናባቱ እኔ ለፍቼ ለማሳድገው ደሞ የስም ባለመብት ደሞ እሱ ሊሆን ነው›› ብለውና ‹‹በገዛ ልጃችንና በገዛ ቋንቋችን ማን ነኪ አለን›› ብለው የሚያወጡ ነው እሚመስለው ፣ እውነቴን እኮ ነው! አስቡት እስቲ ማታለል አወቀ ብሎ ስም ማውጣት እስቲ ምን ይሉታል ፣ በቃ ‹‹ ከኔ ስም ጋር ይግጠም ብያለሁ ይግጠም!›› ይላል አቶ አወቀ ፣ እሱ ሳይሰማ እዛ ቤት ለተወለደው ልጅ ፣ ወንድም ይሁን ሴት ስም አይወጣለትም፣ አቶ አወቀ ‹‹በዘራችን እማይገጥም ስም አውጥተን አናቅም›› እያለ እሚኮፈስ ፣ ያወጣው ስም ለወጣለት ልጅ ይመርበትም አይመርበት ፣ ከሱ ስም ጋር ብቻ ገጥሞ ካየ በቃ ‹‹እንዲህ ናቸው የአውቄ ልጆች አ!›› እያለ በየመንገዱ ጉራውን እሚነዛ ሰው ነው፡፡ ወይ የኛ ሰው ብሎ ብሎ እሚኮራበት ቢያጣ በልጁ ስም መንቀባረር ጀመረ! አይ እኛ አስቂኞቹ……
ወደሌላ ስም እንለፍ አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ፣ ሊያልቅ ሲል ገነነ እሚባሉ መከረኛ ፣ የሆኑ የአባታቸው የአረፍተ ነገር መስሪያ የሆኑ የሚመስለኝ ፣ አንዳንዴም የወላጆጃቸው የማስታወሻ ደብተር ወይም ዲያሪ የሚመስሉኝ ልጆች አሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ወቅት ጠብቀን ለልጆጃችን ስም እንደምናወጣ ሁሉ ፣ ወቅት ጠብቀን ደሞ ብንቀይርላቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ ፣ እኚህ መከረኛ ልጆች በደርግ ጊዜ ፣ በዚያ የኢሀዲግና የደርግ ጦርነት ወቅት ፣ በዚያ በተፋፋመ ጊዜ በመወለዳቸው ፣ ፈርዶባቸው አቶ ገነነም ስም አወጣጥ ይችላሉ መቸም! አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ እና የመጨረሻው የደርግ-ኢሀዲግ ጦርነት ግዜ የተወለደውን ደግሞ ሊያልቅ ሲል ገነነ ብለው ስም አውጥተዋል፡፡ ዛሬ ታዲያ አቶ አብዮት ስሙን አይወደውም ፣ ሆ እውነቱን እኮ ነው ፣ አስቡት እስቲ አብዮት ብሎ አቶ ፣ አሁን በዘመነ ዲሞክራሲ እና በዘመነ ሰላም ሰው ልጁን አብዮት ብሎ ይሰይማል ፣ እሺ ቆይ ያኔስ ጊዜው ነው ፣ ልጁን አብዮት ብሎ ቢሰይም ግድ የለም ፣ አሁን እሺ ያ ዘመን አልፏል አይደለ እንዴ ምናለበት ስሙን ለምሳሌ ከአብዮት ወደ እውቀቱ ፣ ሰላሙ ፣ ፍክክር ምናምን እያሉ ቢያወጡለት እንዴ እውነቴን እኮ ነው ፣ መቸም ከአባት ስም ጋር እንዲገጥም አደል እሚፈለገው ፣ ይኸው ይገጥማል፡- እውቀቱ ገነነ፣ ሰላሙ ገነነ ፣ ፉክክር ገነነ እያሉ መጥራት ይቻል ነበር ታዲያ ምን ያደርጋል የኛ ሰፈር አባቶች አይሰሙም አቦ!
አቶ ገነነም ልክ እንደ አቶ አወቀ ሁሉ ‹‹በህግ አምላክ ካወጣሁልህ ስም ውልፍች ትልና›› እያሉ በቃ ልጆቻቸው በስማቸው አብዮት አብዮት እየሸተቱና እየከረፉ ተሳቀው በመኖር ላይ ናቸው፡፡
በእርግጥ ስለ ስም ስናወራ በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በተለይ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገሮችም ስም ከሁኔታና ከተግባር ጋር ተያይዞ ይወጣል፣ ለምሳሌ ጀርመኖች ሸማኔውን ሸማኔ ፣ እቃ ሻጩን እቃ ሻጭ ብለው የሚጠሩበት አጋጣሚ አለ፣ ሌሎችንም እንዲሁ ብዙ በስራቸውና በሁኔታቸው የሚያወጡበት አጋጣሚ አለ ፣ ማለትም ለምሳሌ ሸማኔውን ዌቨር ፣ ሻጩን ሴለር ምናምን እያሉ ይጠራራሉ ማለት ነው ፣ ይሄን ሰምቼ ታዲያ ዘወር ስል እትዬ ብርጣሉና እማማ ወርቂቱ ግብ ግብ ተያይዘው ደረስኩ ፣ ምነው ምን ሆነው ነው ፣ ምን አጋጫቸው ? ስል የእትዬ ብርጣሉ ልጅ ነው ነገረኛው የእማማ ወርቂቱን ልጅ የሸማኔ ልጅ ብሎ ተሳድቦ ነው አሉኝ! እማማ ወርቂቱ እትዬ ብርጣሉን ‹‹እንዴት ብትንቂኝ ነው በይ ብለሽ ብለሽ ልጅሽን ልከሽ የሸማኔ ልጅ ብለሽ ልጄን እምታሰድቢው እረ!›› ብለው ነጠላቸውን ጥለው ገጠሙ፣ ታዲያ አያችሁ ልዩነት? በጀርመን ሽምንና ከተከበረ ስራም አልፎ የተከበረ ስም ሆኖ ሳለ ወዲህ በኛ ሀገር ግን ንቀት ካዘለ ስድብ ተቆጥሮ ጎረቤት እና ዘር ማንዘር ያጣላል ጉድ ነው ሀበሻ!
ብቻ ግን እንተወውና ሰው መቸም እንደባህሉ ነው እሚኖረው ፣ እንደጀርመኖች ደፋር ሆነን ሸማኔውን ሸማኔ ብለን መሰየም ባንችልም ፣ ባይሆን እንደው ገና ለገና ከአባት ስም ጋር እንዲገጣጠም ብለን እባካችሁ ያልሆነ ስም አናውጣ ተመልከቱ ፡- ሳራ ከች አለ ፣ ቀፋፊው ፊቱ፣ አረግርግ ቆመጡ ብሎ ስም ምን ይሉታል እስቲ!
ሳራ ከች አለ! ብሎ ስም ! መጀመሪያውኑ ከች አለ ብሎ ስም አያስቅም ደረሰ እሚለውን ስም በቦሌ ብሄረሰብ ቋንቋ እ…ከች አለ! ወይ መንቀባረር ከዛ እንዳይገጥም ይሁን እንዲገጥም አይታወቅም በቃ ልጆቻቸውን የሆነ ቃል እየለበጡባቸው ወላጆች ይደበራሉ! አሀሀሀሀ ….አስቂኝ ነገር ነን…ሳራ ከች አለ ከምንል ቢቻል አንዴ ሆኗል መቸም የአባቷን ስም መቀየር አንችልም እንጂ ከች አለ እሚለውን ደረሰ በሚል የሀገሬን ለዛ ያለው ቃል መጠቀም ጥሩ ነበር ግን ምን ዋጋ አለው! አንዴ ሆኗል እሱ ነገር ግን ልጂቷን ለዚህ ስም አጋልጦ ከመስጠት ፣ ከአባቷ ስም ጋር መገጣጠሙ እንደ ህገ መንግስቱ የማይናድ ህግ ከሆነ ምን ይደረጋል ፣ በቃ ሳራ ከማለት ስሰራ ፣ ሳነብ ፣ ወይ ደሞ በዛው በለመዱት በቦሌኛቸው ኬክ ስበላ ፣ ፊልም ሳይ ፣ ጌም ስጫወት ምናምን እሚሉ ስሞችን ሰጥቶ ከሳቅን አይቀር በደንብ መሳቅ ነው፡፡ ከዛ በቃ ከአባቷ ስም ጋር ሲገጣጠም ስሰራ ከች አለ፣ ኬክ ስበላ ከች አለ፣ ፊልም ሳይ ከች አለ! አሁን እስቲ ይሄ ስም ነውን ሆ! ወሬ አረግነውኮ በቃ! መቸም አንዴ በዚህ ሀገር ስም ማውጣት ማለት አረፍተ ነገር መመስረትና አማርኛ ፔረድን እድሜ ልክ መሳተፍ ነውና!....ምን ማድረግ ይቻላል አብረን እንሳቃ…….
አንዴ እንዲሁ በስም ጉዳይ ከሆነ መንገድ ላይ ካገኘሁት ሰው ጋር እያወራን እያለ ፣ አሱ እራሱ በስሙ ሁሌም እንደሚበሳጭ ነገረኝ ፣ ምነው ምን ሆንክ ፣ ማን ነው ስምህ ስል ጠየኩት….
እረ ተወው እሱን አሲቂኝ ነው ስሜ ፣ ካልጠፋ አማርኛ እስቲ በናትህ ብሎ ድንገት እንባው ጥርዝዝ አለ…እንዴ ቆይ እንጂ ይሄን ያህል ምን ቢሆን ነው ስምህ እረ ደስ አይልም እንዳታለቅስ ብዬ በግድ አባብዬ ጠየኩት ስሙን ነገረኝ፣ ስሙ ገፊው ኮስትሬ ነው፡፡ እና አንተ ካስጠላህ አታስቀይርም እንዴ ምን አጨናነቀህ ስለው ፣ ‹‹እሱ አይደለ እንዴ እሚደብረው›› ብሎ ቀጠለ ፣ ‹‹አያቴ የማስቀየር መብቴን ይዞት ሞቷል›› አለኝ ፣ እንዴ እንዴት አይነት ነገር ነው ፣ ጭራሽ የሰው መብትም ይዞ መሞት ይቻላል እንዴ! እረ ይቺ ጉደኛ አገር ብዬ ፣ እንዴት ነው ግን አያትህ የማስቀየር መብትህን ይዘውት የሞቱት ፣ መብት አይደለም የሰው ልጁ ልብሱንና ወርቁን ሳይቀር ሲሞት እዚህ ትቶ አይደለ እንዴ እሚቀበረው አልኩት፣ ‹‹አይ አንተ ጥሩ ብለሀል›› ብሎ ቀጠለ ‹‹ይሄ እኮ ባይን የማይታይ የአደራ ቃል ነው ፣ በቃ ማንም የልጅ ልጄ እኔ ስም አውጥቼለት ፣ ደስ ሳይለው ቀርቶ አስቀይሮ አያውቅም፣ እና አደራ ብየሀለው ልጄ ፣ ካስቀየርክ በአዲስ ስምህ ትሞታለህ ፣ ኑሮ አይቀናህም ፣ ብሎ እርግማንም ትንቢትም ቀላቅሎ ነው ነገሮኝ የሞተው ስለዚህ ቃሉን ብሽር ትንቢቱና እርግማኑ የሚደርስ ስለሚመስለኝ እፈራለሁ ፣ እና ይኸው አሁን ማንም ገፌ ፣ ገፎ ፣ ገፊቲ እያሉ ቁልምጫ አይሉት ስድብ እየተጠራሁበት እገኛለው›› ብሎ አጫወተኝ፡፡
አንዳንዴ ደሞ የሚያስቀው ነገር፣ መቸም አንዴ ስለስም ከተነሳ ብዬ ነው ፣ በቃ የሆነ የውጭ ሀገር ስም ነገር ከሆነ ደስታችን አይጣል ነው፣ እነ ዮሀንሶች ጆን ሲባሉ ደስታቸው አይጣል ነው! ፣ እነ ሮቤል ሮበርት ሲባሉ ይፈነድቃሉ! ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ብዙ ብዙ ግን ለምን ፣ አንዱ ጓደኛዬ ምርር ብሎት ያደለውማ ሪሀና ራውል ይባላል እኔ አለው እንጂ ለቁልምጫ እንኳን እማይመች አረገሀኝ እሚል ስም ይዤ ወይኔ! ሆ ብቻ የሆነ ብዙ አስቂኝ ነገር አለው ፣ በመጨረሻ ግን የበኩሌን ልምከራችሁ ፣ አንዳንዴ እኮ ከወጣትም ምክር መቀበል ብፁእነት ነው ፣ እና እኔ እምለው ምን መሰላችሁ ስም ስታወጡ በተለይ ለወላጆች የናንተን ታሪክ እንዲወክል ብቻ አታስገድዱ እሺ ግን ይሄም ይሁን ነገር ግን ልጁ ሲያድግ የመቀየር መብት ይኖረው ዘንድ ህገ መንግስታችሁን ወይንም ህገ ስማችሁን ተቀያሪ ፍሌክሴብል አድርጉት እንጂ ባለፈ ትውልድ እና መንግስት አሰያየም የወጣውን ስም ተሸክሞ የመኖር ግዴታ ያለበት ልጅ የለም፡፡በዚህ እግር ምናለበት መጥፋት የሌለባቸው ስንት ሺህ ቋሚ ቅርሶች አሉን አይደለ እንዴ ፣ እነሱን ካፈረስክ ወዮልክ ብላችሁ ለምን ቃል አስገብታችሁ አትሞቱም!.....አበቃሁ፡፡
ሲገናኝ
…………..
በካሌብ(ስንታየሁ)አለማየሁ

’’ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው’’ ይባል የለ ፣ ጓደኞቼም እንዲሁ አስተኔ ህይወት ገጥሟቸዋል፣ ማለትም ፣ አንደኛው ሲጋራ ፋብሪካ ፣ አንዱ አረቄ ፋብሪካ እንዲሁም ሌላኛው ደግሞ ሆቴል ውስጥ ስራ ተቀጥረዋል፡፡ ታዲያ ’’ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው’’ እንድል ያስባለኝ ነገር ቢኖር ፣ ሲጋራ ፋብሪካ የተቀጠረው ጓደኛዬ እጅግ ሲበዛ የሲጋራ ሱስ ያለበት ፣ ገና ፊቱን ሲያዩ የሆነ የሱስ ኩይሳ ያለበት እሚመስል ሰው ነው ፣ አጅሬው እና ሲጋራ ዳግም ተገናኙ ዋው ፣ እንደተቀጠረ ደወለልኝና ‹‹ እልልል…..ጓደኛዬ ደስ ይበልህ ደስ ብሎኛል አለኝ›› እንዴት ነው አሪፍ ደመወዝ አለው እንዴ ? ስለው ‹‹ እንዴ እረ ከደሙዙ በላይ ጥቅማጥቅሙ ነው ጮቤ ያስረገጠኝ ጀለሴ›› ምን ተገኘ ደሞ? አልኩ ተረጋግቼ ‹‹ በወር እያንዳንዱ ሰው አራት አራት ፓኬት ሲጋራ በነፃ ይሰጠዋል ፣ ነገር ግን እኔ ደግሞ ሀላፊ ስለምሆን ለኔ ሰባት ፓኬት ተፈቅዶልኛል እና ይሄ አያስደስትም ›› አለኝ እየተፍለቀለቀ ፣ …..አሰብኩት ይህ ሰው መቸም ማጨስ እስካላቆመ ድረስ እና ለዚህ ለማይረባ ነገር በየቀኑ ገንዘቡን ከሚከሰክስ ፣ ባይሆን በነፃ ማግኘቱ ጥሩ ነው ፣ እሱ እንኳን ደስ ያለን ብሎ ሲነግረኝ ነገር ግን እኔ በጣም አዘንኩ ፣ ሞቻለሁ ብሎ የነገረኝ ነው የመሰለኝ ፣ አጠገቤ በረኪና አስቀምጨ ልጠጣው ነው ያለኝ ነው የመሰለኝ ፣ አስቡት እስቲ ገንዘብ በሌላው ሰአት አንድ ፓኬት በቀን የሚምግ ጀግና አሁን ሰባት ሰጥተውት ጭራሽ ቶሎ ሙትልን ፣ ወግድልን አንይህ ይመስላል እኮ ጎበዝ….አራዳ ጉራጌ ቢሆን ኖሮ በየወሩ የሚያገኛትን ሲጃራ አትርፎ ይነግድባት ነበር….ለማንኛውም ግን ለሱሰኛም አምላክ አለውና ስራ ሰሪው ወይንም ደግሞ ጭስ እና አጫሹ ተገናኝተዋል፡፡
‹‹አረቄ ፋብሪካ ምን እንደሚገጨን ታውቂያለሽ ?›› አለኝ ይሄኛው ሞዛዛ ጓደኛዬ ደግሞ በቁሙ የአረቄ ቦይ ታውቃላችሁ እንደዛ ሆኗል፡፡ በቃ ጠዋት ተነስቶ እሷን ፉት ካላለ አይነቃም ፣ ባገኛት አጋጣሚ ሁሉ በቃ መለጋት ፣ መለጋት ነው ስራው ደሞ እኮ ወገኞች ያ ሲጋራ እሚምገውና ይቺ አረቂ ፉት እምትለው ጀለሴ ሲፎጋገሩ ! ፣ የሆነ ቀን ይቺ ፉት እምትለዋ ጭስ ነገር አልወድም ምናምን ብላ የሷ አረቄ ግን ቅዱስ ተግባር እንደሆነ እምትቆጥረው ፣ የሆነ ሳይኖራት ተበድራ ተጠቃቅማ ምናምን ቀብረር ነገር እምትለዋ ፣ ቀንዳም ሱሳሟ ጓደኛዬ ባይ ዘ ወይ ያው እንደኔ አጭር ቀጭን ስለሆነች ነው አንቺ እያልን በሴት ስም የምንጠራት እንጂ ከወንድም ወንድ ናት ሌላው ሌላው ላይ ማለቴ ነው! ‹‹ ቆይ አንተ ለምን ሱስ አታቆምም ፣ አይደብርህም እንዴ ! እኛስ ይቺን ነገር ፉት ብንል ተፅፎልን ነው ! እንዴ እውነቴን እኮ ነው ፣ አቁም እስቲ አፍህን ምድጃ አታርገው በናትህ›› ምናምን ብላ ጀለሴ አጫሹ ላይ ጉራዋን አጨሰችበት ፣ አሀሀሀሀይ ወገኞች እረ አታስቁኝ አልሸሹም ዘወር አሉ ነገር እኮ ነው ጭውቴው ‹‹ቆይ ምን ተብሎ ነው ላንተ የተፃፈልህ ባክህ ፣ ማን ነው ደሞ የፃፈልህ ፣ የት ላይ ነው የተፃፈልህ ደግሞ ሆ?›› አላት ይቺን ጉረኛ ጓደኛዬን ፣ ታዲያ ሁለቱም በሙሉ ትጥቅ ሁነው ነው እንዲህ እሚነታረኩት ፣ በሙሉ ትጥቅ ስል ያው ቀጮም ከአረቂዋ ጋር ፣ እሱም ከሲጋራው ጋር ሆነው ነው ማለቴ ነው ካልገባችሁ፡፡ ከዛ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው ይቺ ጉረኛ ፈላስፋ እሷ እሚሉ ፈላስፋ እና አንባቢ ደግሞ ኤዲያ….‹‹ ስማ ወይን ያስተፈስኪ ይለዋል አምላክ በቃሉ ፣ እና እኔ ደግሞ ወይን መግዛት ያልቻልኩት ፣ ፒን ያስተፈስኪ ብዬ አረቂዬን እጨልጣለሁሁሁ አሀሀሀሀሀ ፣ ሞኞ ›› ምናምን ብላ ሙድ ያዘችበት ፣ መፅሀፍ ቅዱስን ተሳፈጠች አይገልፀውም! ይቺ ቀጫጫ !.....
እናላችሁ ያው አረቄ ፋብሪካ ገጠመው ለዚህኛውም አረቂያም ጓደኛዬ! በቃ መቸስ እግዜር የከፈተውን ….አይደል ተረቱ….እግዜር ባያመጣውም ሱሱን ፣ ያው ለሱሰኛም ሱሰኛ መስሪያ ቤት ተፈጥሯል መሰለኝ ፣ እንደየፊናቸው እና እንደየተሰጧቸው በየመስሪያ ቤቱ ተሰገሰጉ ‹‹ ‹‹አረቄ ፋብሪካ ምን እንደሚገጨን ታውቂያለሽ ?›› አለኝ ፣ እረ አላውቅም ‹‹ በየወሩ ሉክ! በየወሩ እ…ስድስት ስድስት ጠርሙስ አረቄ ይገጨናል ፣ እኔ ደግሞ እ…ሀላፊ መሆኔን አስመልክቶ ከአንድ ቮድካ ጋር ዱቅ ይደረግልኛልልልል ፣ አሁን ያዝ ከእግዜር ውሀህ ጋር ችርስ አቦ!›› አለኝ በደስታ ፣ አሁንም እኔ ግን አዘንኩ ፣ ከነበራቸው ቀንድ ያወጣ ሱስ ላይ ጥቅማ ጥቅም ብሎ ይሄንን የመሰለ ሰይጣን ተግባር መፈፀም ፣ በቃ ሰርክ ሳገኛቸው ጓደኞቼን አጭሰው ከስለው ፣ ጠጥተው ሰክረው ፣ ሌሎቹማ ስንቶቹ ቤት ሰርተው ሰርተው ፣ አከራይተው አፈናጠው ምናምን እኚህ የኔዎቹ ፣ ሱሳቸው እንጂ ህልማቸው ላይ መፈናጠጥ አልቻሉም ፣ በቃ ስናወራ ብትሰሙ ህልማቸው ሌላ ፣ መዋያቸው ሌላ ….ፍየል ወዲያ …..ቅዝምዝም….ምናምን ብቻ በቃ …ለነገሩ እኔም ብሆን ህልሜን አልኖርኩም ግን ምንም ቢሆን በጣም በጥቂቱም ቢሆን ከነሱ እምሻለው ፣ ይቺኑ ጥቂት ህልም በአረቄ ምናምን አላጠብኳትም አሁንም አብራኝ አለች፡፡
የዚህኛው ሱስ ደግሞ ለየት ይላል ፣ የዚህን ሱስ እንኳን እኔም ቢይዘኝ የት በደረስኩ ያልኩበት ነበር ፣ የዚህኛው ጓደኛዬ ሱስ ምግብ ነው ታድሎ ነገር ግን ለዚህ አገር አይሆንም ምናምን እሚሉ የደሀ አመለካከቶችና ነቆራዎች ይደርሱታል ፣ ግን በልቶም ያስመሰክራል እኮ ፣ እኔ ፀጉሬን እያሻሸው ስወጣ ትዝ ይለኛል ገና ከህፃንነታችን እሱ ሁዱን እያሸ ነበር ብይ ለመጫወት እምንጠራራው ፣ በቃ የሆነ ሲያድግ እራሱ በደንብ እንዲበላ ይመስላል ፣ ከሌሎች ኢትዮጲያውያን ቤት በተለየ እነሱ ቤት ስለ ምግብ በደንብ ይተረት ነበር ፣ እነ ካንጀት ካዘኑ …….፣ እነ ሆድ ያባውን………፣ እነ ሲበሉ የላኩት ብቻ ምን አለፋቹ በቃ በሆድ ዙሪያ የተነገሩ ሁላ እነሱ ቤት ተፅፈዋል ፣ ሆዳም ሁላ!
እና ይሄ የሆድ አባት የእህል አፈንፋኝ ፣ አድሉ እያሸተተች ሄዳ ሆቴል እንዲቀጠር አደረገችው ፣ በቃ ከምንጩ ተጣደበት ነው ያሉት የሰፈር ሰው ሁላ ፣ ‹‹በስማም እንግዲህ በምግብ ሊጠመቅ ነው በሉኛ ›› አሉ እማማ እንትና አፋቸውን አጣመው ሆ ፣ እሱ ለጎረሰ የሳቸው አፍ ማጣመም እስቲ ምን ይባላል ፣ አይ አበሻ እንደው ፣ አስቂኝ ነገሮች ነን አንዳንዴ!
እና እንደፈረደብኝ ይሄም መጥቶ ስራ ሲቀጠር ነገረኝ ፣ እኔ ይኸው እነሱ ስራ ይቀጠራሉ ፣ ይቀጠራሉ ፣ ሱሰኞቹ እንኳን ስራ አግኝተው እኔ በቃ ይሄው ቁጭ ብዬ እነሱን መምከር ሆኗል ስራዬ ፣ አንድ ቀን ግን የጤነኞችም አምላክ ፣ ለኔም ያሽረኝ ይሆናል፡፡ እና ያው እንዳልኳችሁ የዚህኛው ጥቅማጥቅም ደግሞ በቃ መብላት ነው ‹‹ ቁርስም ፣ ምሳም ፣ እራትም የሚችል ሆቴል አይተህ ታቃለህ? ለነገሩ አንተ እንዴት ታያለህ ፣ የተማርከው መረጃ ምናምን ምግብ በዞረበት እማይዞር ፣ እየውልሽ እኔ የሆዴ አምላክ ፣ ስንት ሺኅ ክትፎ በሚዛቅበት ፣ ስንት ሺኅ በቃ የምግብ አይነት በሚፈተትበት ማህሌት ውስጥ እኑር አረገኝ ፈጣሪ እና ያመጣልኝን እየበላሁ መኖር ነዋ›› አለኝ ፣ እኔ እንዲያ ሲነግረኝ እራሱ ገና ማስታወቂያ ሳይ ውዬ አረፍ ማለቴ ነበር ምሳ እንኳን አልበላሁም ፣ ተመልከቱ እስቲ ታዲያ በይ እና ተበይ ፣ ጭስ እና አጫሽ ፣ መጠጥ እና ጠጪ ሲገናኙ ስራ ለሰሪው አያሰኝም ….ምናለበት እንዲህ ሁላችንንም በምንፈልገው ቦታ ቢቀጥረን ….አይዟችሁ አይቀርም ፣ ግን ሱስን ወዲያ ፣ አስቡት እስቲ የሰው ልጅን ያህል ታላቅ አሳቢና አገናዛቢ ፍጥረት ፣የምን በሆነ ግኡዝ ነገር ፣ሱስ ተይዞ መጠፍነግ ነው ፣ እረ ላሽ!