Thursday, December 12, 2013

ስምና ሁናቴ
…………….
በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

ስም ያው ብዙ ጊዜ መጠሪያ ነው ፣ አንዳንዶቹ ወላጆች ከሁኔታዎች ጋር እያመሳሰሉ ያወጣሉ ፣ አንዳንዶቹ አፋቸው ላይ የመጣውን ደስ ያላቸውን ስያሜ ይሰጡበታል፡፡ በእኛ ሀገር በተለይ አፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ በሆነበት አካባቢ ስሞቻችን አንዳንድ ግዜ ከአባት ስም ጋር ተገጣጥሞ ትርጉም እንዲሰጥ ፣ እንዲገጥም ፣ መልክት እንዲያስተላልፍ ፣ አንዳንድ ጊዜ ደሞ ተረት መተረቻም ቅኔ መቀኛም ያደርጉታል፡፡ 
ለምሳሌ እኛ ሰፈር የነበረ አቶ አወቀ የሚባል ሰውዬ ፣ የልጆቹን ስም ከሱ ስም ጋር እንዲገጥም አድርጎነው ያወጣሁ፣ መቅደም አወቀ፣ መስጠት አወቀ፣ ወ/ሪት ማታለል አወቀ፣ መሳቅ አወቀ፣ እና ወላጆች አንዳንዴ ሳስበው ለነሱ ከነሱ ጋር የሚሄድ ስም ይሁን እንጂ ምንም አይነት ቃል ይሁን በቃ ዝም ብለው ይለጥፉብናል ፣ በቃ ‹‹ምናባቱ እኔ ለፍቼ ለማሳድገው ደሞ የስም ባለመብት ደሞ እሱ ሊሆን ነው›› ብለውና ‹‹በገዛ ልጃችንና በገዛ ቋንቋችን ማን ነኪ አለን›› ብለው የሚያወጡ ነው እሚመስለው ፣ እውነቴን እኮ ነው! አስቡት እስቲ ማታለል አወቀ ብሎ ስም ማውጣት እስቲ ምን ይሉታል ፣ በቃ ‹‹ ከኔ ስም ጋር ይግጠም ብያለሁ ይግጠም!›› ይላል አቶ አወቀ ፣ እሱ ሳይሰማ እዛ ቤት ለተወለደው ልጅ ፣ ወንድም ይሁን ሴት ስም አይወጣለትም፣ አቶ አወቀ ‹‹በዘራችን እማይገጥም ስም አውጥተን አናቅም›› እያለ እሚኮፈስ ፣ ያወጣው ስም ለወጣለት ልጅ ይመርበትም አይመርበት ፣ ከሱ ስም ጋር ብቻ ገጥሞ ካየ በቃ ‹‹እንዲህ ናቸው የአውቄ ልጆች አ!›› እያለ በየመንገዱ ጉራውን እሚነዛ ሰው ነው፡፡ ወይ የኛ ሰው ብሎ ብሎ እሚኮራበት ቢያጣ በልጁ ስም መንቀባረር ጀመረ! አይ እኛ አስቂኞቹ……
ወደሌላ ስም እንለፍ አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ፣ ሊያልቅ ሲል ገነነ እሚባሉ መከረኛ ፣ የሆኑ የአባታቸው የአረፍተ ነገር መስሪያ የሆኑ የሚመስለኝ ፣ አንዳንዴም የወላጆጃቸው የማስታወሻ ደብተር ወይም ዲያሪ የሚመስሉኝ ልጆች አሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ወቅት ጠብቀን ለልጆጃችን ስም እንደምናወጣ ሁሉ ፣ ወቅት ጠብቀን ደሞ ብንቀይርላቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ ፣ እኚህ መከረኛ ልጆች በደርግ ጊዜ ፣ በዚያ የኢሀዲግና የደርግ ጦርነት ወቅት ፣ በዚያ በተፋፋመ ጊዜ በመወለዳቸው ፣ ፈርዶባቸው አቶ ገነነም ስም አወጣጥ ይችላሉ መቸም! አብዮት ገነነ ፣ እሳቱ ገነነ እና የመጨረሻው የደርግ-ኢሀዲግ ጦርነት ግዜ የተወለደውን ደግሞ ሊያልቅ ሲል ገነነ ብለው ስም አውጥተዋል፡፡ ዛሬ ታዲያ አቶ አብዮት ስሙን አይወደውም ፣ ሆ እውነቱን እኮ ነው ፣ አስቡት እስቲ አብዮት ብሎ አቶ ፣ አሁን በዘመነ ዲሞክራሲ እና በዘመነ ሰላም ሰው ልጁን አብዮት ብሎ ይሰይማል ፣ እሺ ቆይ ያኔስ ጊዜው ነው ፣ ልጁን አብዮት ብሎ ቢሰይም ግድ የለም ፣ አሁን እሺ ያ ዘመን አልፏል አይደለ እንዴ ምናለበት ስሙን ለምሳሌ ከአብዮት ወደ እውቀቱ ፣ ሰላሙ ፣ ፍክክር ምናምን እያሉ ቢያወጡለት እንዴ እውነቴን እኮ ነው ፣ መቸም ከአባት ስም ጋር እንዲገጥም አደል እሚፈለገው ፣ ይኸው ይገጥማል፡- እውቀቱ ገነነ፣ ሰላሙ ገነነ ፣ ፉክክር ገነነ እያሉ መጥራት ይቻል ነበር ታዲያ ምን ያደርጋል የኛ ሰፈር አባቶች አይሰሙም አቦ!
አቶ ገነነም ልክ እንደ አቶ አወቀ ሁሉ ‹‹በህግ አምላክ ካወጣሁልህ ስም ውልፍች ትልና›› እያሉ በቃ ልጆቻቸው በስማቸው አብዮት አብዮት እየሸተቱና እየከረፉ ተሳቀው በመኖር ላይ ናቸው፡፡
በእርግጥ ስለ ስም ስናወራ በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በተለይ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገሮችም ስም ከሁኔታና ከተግባር ጋር ተያይዞ ይወጣል፣ ለምሳሌ ጀርመኖች ሸማኔውን ሸማኔ ፣ እቃ ሻጩን እቃ ሻጭ ብለው የሚጠሩበት አጋጣሚ አለ፣ ሌሎችንም እንዲሁ ብዙ በስራቸውና በሁኔታቸው የሚያወጡበት አጋጣሚ አለ ፣ ማለትም ለምሳሌ ሸማኔውን ዌቨር ፣ ሻጩን ሴለር ምናምን እያሉ ይጠራራሉ ማለት ነው ፣ ይሄን ሰምቼ ታዲያ ዘወር ስል እትዬ ብርጣሉና እማማ ወርቂቱ ግብ ግብ ተያይዘው ደረስኩ ፣ ምነው ምን ሆነው ነው ፣ ምን አጋጫቸው ? ስል የእትዬ ብርጣሉ ልጅ ነው ነገረኛው የእማማ ወርቂቱን ልጅ የሸማኔ ልጅ ብሎ ተሳድቦ ነው አሉኝ! እማማ ወርቂቱ እትዬ ብርጣሉን ‹‹እንዴት ብትንቂኝ ነው በይ ብለሽ ብለሽ ልጅሽን ልከሽ የሸማኔ ልጅ ብለሽ ልጄን እምታሰድቢው እረ!›› ብለው ነጠላቸውን ጥለው ገጠሙ፣ ታዲያ አያችሁ ልዩነት? በጀርመን ሽምንና ከተከበረ ስራም አልፎ የተከበረ ስም ሆኖ ሳለ ወዲህ በኛ ሀገር ግን ንቀት ካዘለ ስድብ ተቆጥሮ ጎረቤት እና ዘር ማንዘር ያጣላል ጉድ ነው ሀበሻ!
ብቻ ግን እንተወውና ሰው መቸም እንደባህሉ ነው እሚኖረው ፣ እንደጀርመኖች ደፋር ሆነን ሸማኔውን ሸማኔ ብለን መሰየም ባንችልም ፣ ባይሆን እንደው ገና ለገና ከአባት ስም ጋር እንዲገጣጠም ብለን እባካችሁ ያልሆነ ስም አናውጣ ተመልከቱ ፡- ሳራ ከች አለ ፣ ቀፋፊው ፊቱ፣ አረግርግ ቆመጡ ብሎ ስም ምን ይሉታል እስቲ!
ሳራ ከች አለ! ብሎ ስም ! መጀመሪያውኑ ከች አለ ብሎ ስም አያስቅም ደረሰ እሚለውን ስም በቦሌ ብሄረሰብ ቋንቋ እ…ከች አለ! ወይ መንቀባረር ከዛ እንዳይገጥም ይሁን እንዲገጥም አይታወቅም በቃ ልጆቻቸውን የሆነ ቃል እየለበጡባቸው ወላጆች ይደበራሉ! አሀሀሀሀ ….አስቂኝ ነገር ነን…ሳራ ከች አለ ከምንል ቢቻል አንዴ ሆኗል መቸም የአባቷን ስም መቀየር አንችልም እንጂ ከች አለ እሚለውን ደረሰ በሚል የሀገሬን ለዛ ያለው ቃል መጠቀም ጥሩ ነበር ግን ምን ዋጋ አለው! አንዴ ሆኗል እሱ ነገር ግን ልጂቷን ለዚህ ስም አጋልጦ ከመስጠት ፣ ከአባቷ ስም ጋር መገጣጠሙ እንደ ህገ መንግስቱ የማይናድ ህግ ከሆነ ምን ይደረጋል ፣ በቃ ሳራ ከማለት ስሰራ ፣ ሳነብ ፣ ወይ ደሞ በዛው በለመዱት በቦሌኛቸው ኬክ ስበላ ፣ ፊልም ሳይ ፣ ጌም ስጫወት ምናምን እሚሉ ስሞችን ሰጥቶ ከሳቅን አይቀር በደንብ መሳቅ ነው፡፡ ከዛ በቃ ከአባቷ ስም ጋር ሲገጣጠም ስሰራ ከች አለ፣ ኬክ ስበላ ከች አለ፣ ፊልም ሳይ ከች አለ! አሁን እስቲ ይሄ ስም ነውን ሆ! ወሬ አረግነውኮ በቃ! መቸም አንዴ በዚህ ሀገር ስም ማውጣት ማለት አረፍተ ነገር መመስረትና አማርኛ ፔረድን እድሜ ልክ መሳተፍ ነውና!....ምን ማድረግ ይቻላል አብረን እንሳቃ…….
አንዴ እንዲሁ በስም ጉዳይ ከሆነ መንገድ ላይ ካገኘሁት ሰው ጋር እያወራን እያለ ፣ አሱ እራሱ በስሙ ሁሌም እንደሚበሳጭ ነገረኝ ፣ ምነው ምን ሆንክ ፣ ማን ነው ስምህ ስል ጠየኩት….
እረ ተወው እሱን አሲቂኝ ነው ስሜ ፣ ካልጠፋ አማርኛ እስቲ በናትህ ብሎ ድንገት እንባው ጥርዝዝ አለ…እንዴ ቆይ እንጂ ይሄን ያህል ምን ቢሆን ነው ስምህ እረ ደስ አይልም እንዳታለቅስ ብዬ በግድ አባብዬ ጠየኩት ስሙን ነገረኝ፣ ስሙ ገፊው ኮስትሬ ነው፡፡ እና አንተ ካስጠላህ አታስቀይርም እንዴ ምን አጨናነቀህ ስለው ፣ ‹‹እሱ አይደለ እንዴ እሚደብረው›› ብሎ ቀጠለ ፣ ‹‹አያቴ የማስቀየር መብቴን ይዞት ሞቷል›› አለኝ ፣ እንዴ እንዴት አይነት ነገር ነው ፣ ጭራሽ የሰው መብትም ይዞ መሞት ይቻላል እንዴ! እረ ይቺ ጉደኛ አገር ብዬ ፣ እንዴት ነው ግን አያትህ የማስቀየር መብትህን ይዘውት የሞቱት ፣ መብት አይደለም የሰው ልጁ ልብሱንና ወርቁን ሳይቀር ሲሞት እዚህ ትቶ አይደለ እንዴ እሚቀበረው አልኩት፣ ‹‹አይ አንተ ጥሩ ብለሀል›› ብሎ ቀጠለ ‹‹ይሄ እኮ ባይን የማይታይ የአደራ ቃል ነው ፣ በቃ ማንም የልጅ ልጄ እኔ ስም አውጥቼለት ፣ ደስ ሳይለው ቀርቶ አስቀይሮ አያውቅም፣ እና አደራ ብየሀለው ልጄ ፣ ካስቀየርክ በአዲስ ስምህ ትሞታለህ ፣ ኑሮ አይቀናህም ፣ ብሎ እርግማንም ትንቢትም ቀላቅሎ ነው ነገሮኝ የሞተው ስለዚህ ቃሉን ብሽር ትንቢቱና እርግማኑ የሚደርስ ስለሚመስለኝ እፈራለሁ ፣ እና ይኸው አሁን ማንም ገፌ ፣ ገፎ ፣ ገፊቲ እያሉ ቁልምጫ አይሉት ስድብ እየተጠራሁበት እገኛለው›› ብሎ አጫወተኝ፡፡
አንዳንዴ ደሞ የሚያስቀው ነገር፣ መቸም አንዴ ስለስም ከተነሳ ብዬ ነው ፣ በቃ የሆነ የውጭ ሀገር ስም ነገር ከሆነ ደስታችን አይጣል ነው፣ እነ ዮሀንሶች ጆን ሲባሉ ደስታቸው አይጣል ነው! ፣ እነ ሮቤል ሮበርት ሲባሉ ይፈነድቃሉ! ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ብዙ ብዙ ግን ለምን ፣ አንዱ ጓደኛዬ ምርር ብሎት ያደለውማ ሪሀና ራውል ይባላል እኔ አለው እንጂ ለቁልምጫ እንኳን እማይመች አረገሀኝ እሚል ስም ይዤ ወይኔ! ሆ ብቻ የሆነ ብዙ አስቂኝ ነገር አለው ፣ በመጨረሻ ግን የበኩሌን ልምከራችሁ ፣ አንዳንዴ እኮ ከወጣትም ምክር መቀበል ብፁእነት ነው ፣ እና እኔ እምለው ምን መሰላችሁ ስም ስታወጡ በተለይ ለወላጆች የናንተን ታሪክ እንዲወክል ብቻ አታስገድዱ እሺ ግን ይሄም ይሁን ነገር ግን ልጁ ሲያድግ የመቀየር መብት ይኖረው ዘንድ ህገ መንግስታችሁን ወይንም ህገ ስማችሁን ተቀያሪ ፍሌክሴብል አድርጉት እንጂ ባለፈ ትውልድ እና መንግስት አሰያየም የወጣውን ስም ተሸክሞ የመኖር ግዴታ ያለበት ልጅ የለም፡፡በዚህ እግር ምናለበት መጥፋት የሌለባቸው ስንት ሺህ ቋሚ ቅርሶች አሉን አይደለ እንዴ ፣ እነሱን ካፈረስክ ወዮልክ ብላችሁ ለምን ቃል አስገብታችሁ አትሞቱም!.....አበቃሁ፡፡
ሲገናኝ
…………..
በካሌብ(ስንታየሁ)አለማየሁ

’’ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው’’ ይባል የለ ፣ ጓደኞቼም እንዲሁ አስተኔ ህይወት ገጥሟቸዋል፣ ማለትም ፣ አንደኛው ሲጋራ ፋብሪካ ፣ አንዱ አረቄ ፋብሪካ እንዲሁም ሌላኛው ደግሞ ሆቴል ውስጥ ስራ ተቀጥረዋል፡፡ ታዲያ ’’ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው’’ እንድል ያስባለኝ ነገር ቢኖር ፣ ሲጋራ ፋብሪካ የተቀጠረው ጓደኛዬ እጅግ ሲበዛ የሲጋራ ሱስ ያለበት ፣ ገና ፊቱን ሲያዩ የሆነ የሱስ ኩይሳ ያለበት እሚመስል ሰው ነው ፣ አጅሬው እና ሲጋራ ዳግም ተገናኙ ዋው ፣ እንደተቀጠረ ደወለልኝና ‹‹ እልልል…..ጓደኛዬ ደስ ይበልህ ደስ ብሎኛል አለኝ›› እንዴት ነው አሪፍ ደመወዝ አለው እንዴ ? ስለው ‹‹ እንዴ እረ ከደሙዙ በላይ ጥቅማጥቅሙ ነው ጮቤ ያስረገጠኝ ጀለሴ›› ምን ተገኘ ደሞ? አልኩ ተረጋግቼ ‹‹ በወር እያንዳንዱ ሰው አራት አራት ፓኬት ሲጋራ በነፃ ይሰጠዋል ፣ ነገር ግን እኔ ደግሞ ሀላፊ ስለምሆን ለኔ ሰባት ፓኬት ተፈቅዶልኛል እና ይሄ አያስደስትም ›› አለኝ እየተፍለቀለቀ ፣ …..አሰብኩት ይህ ሰው መቸም ማጨስ እስካላቆመ ድረስ እና ለዚህ ለማይረባ ነገር በየቀኑ ገንዘቡን ከሚከሰክስ ፣ ባይሆን በነፃ ማግኘቱ ጥሩ ነው ፣ እሱ እንኳን ደስ ያለን ብሎ ሲነግረኝ ነገር ግን እኔ በጣም አዘንኩ ፣ ሞቻለሁ ብሎ የነገረኝ ነው የመሰለኝ ፣ አጠገቤ በረኪና አስቀምጨ ልጠጣው ነው ያለኝ ነው የመሰለኝ ፣ አስቡት እስቲ ገንዘብ በሌላው ሰአት አንድ ፓኬት በቀን የሚምግ ጀግና አሁን ሰባት ሰጥተውት ጭራሽ ቶሎ ሙትልን ፣ ወግድልን አንይህ ይመስላል እኮ ጎበዝ….አራዳ ጉራጌ ቢሆን ኖሮ በየወሩ የሚያገኛትን ሲጃራ አትርፎ ይነግድባት ነበር….ለማንኛውም ግን ለሱሰኛም አምላክ አለውና ስራ ሰሪው ወይንም ደግሞ ጭስ እና አጫሹ ተገናኝተዋል፡፡
‹‹አረቄ ፋብሪካ ምን እንደሚገጨን ታውቂያለሽ ?›› አለኝ ይሄኛው ሞዛዛ ጓደኛዬ ደግሞ በቁሙ የአረቄ ቦይ ታውቃላችሁ እንደዛ ሆኗል፡፡ በቃ ጠዋት ተነስቶ እሷን ፉት ካላለ አይነቃም ፣ ባገኛት አጋጣሚ ሁሉ በቃ መለጋት ፣ መለጋት ነው ስራው ደሞ እኮ ወገኞች ያ ሲጋራ እሚምገውና ይቺ አረቂ ፉት እምትለው ጀለሴ ሲፎጋገሩ ! ፣ የሆነ ቀን ይቺ ፉት እምትለዋ ጭስ ነገር አልወድም ምናምን ብላ የሷ አረቄ ግን ቅዱስ ተግባር እንደሆነ እምትቆጥረው ፣ የሆነ ሳይኖራት ተበድራ ተጠቃቅማ ምናምን ቀብረር ነገር እምትለዋ ፣ ቀንዳም ሱሳሟ ጓደኛዬ ባይ ዘ ወይ ያው እንደኔ አጭር ቀጭን ስለሆነች ነው አንቺ እያልን በሴት ስም የምንጠራት እንጂ ከወንድም ወንድ ናት ሌላው ሌላው ላይ ማለቴ ነው! ‹‹ ቆይ አንተ ለምን ሱስ አታቆምም ፣ አይደብርህም እንዴ ! እኛስ ይቺን ነገር ፉት ብንል ተፅፎልን ነው ! እንዴ እውነቴን እኮ ነው ፣ አቁም እስቲ አፍህን ምድጃ አታርገው በናትህ›› ምናምን ብላ ጀለሴ አጫሹ ላይ ጉራዋን አጨሰችበት ፣ አሀሀሀሀይ ወገኞች እረ አታስቁኝ አልሸሹም ዘወር አሉ ነገር እኮ ነው ጭውቴው ‹‹ቆይ ምን ተብሎ ነው ላንተ የተፃፈልህ ባክህ ፣ ማን ነው ደሞ የፃፈልህ ፣ የት ላይ ነው የተፃፈልህ ደግሞ ሆ?›› አላት ይቺን ጉረኛ ጓደኛዬን ፣ ታዲያ ሁለቱም በሙሉ ትጥቅ ሁነው ነው እንዲህ እሚነታረኩት ፣ በሙሉ ትጥቅ ስል ያው ቀጮም ከአረቂዋ ጋር ፣ እሱም ከሲጋራው ጋር ሆነው ነው ማለቴ ነው ካልገባችሁ፡፡ ከዛ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው ይቺ ጉረኛ ፈላስፋ እሷ እሚሉ ፈላስፋ እና አንባቢ ደግሞ ኤዲያ….‹‹ ስማ ወይን ያስተፈስኪ ይለዋል አምላክ በቃሉ ፣ እና እኔ ደግሞ ወይን መግዛት ያልቻልኩት ፣ ፒን ያስተፈስኪ ብዬ አረቂዬን እጨልጣለሁሁሁ አሀሀሀሀሀ ፣ ሞኞ ›› ምናምን ብላ ሙድ ያዘችበት ፣ መፅሀፍ ቅዱስን ተሳፈጠች አይገልፀውም! ይቺ ቀጫጫ !.....
እናላችሁ ያው አረቄ ፋብሪካ ገጠመው ለዚህኛውም አረቂያም ጓደኛዬ! በቃ መቸስ እግዜር የከፈተውን ….አይደል ተረቱ….እግዜር ባያመጣውም ሱሱን ፣ ያው ለሱሰኛም ሱሰኛ መስሪያ ቤት ተፈጥሯል መሰለኝ ፣ እንደየፊናቸው እና እንደየተሰጧቸው በየመስሪያ ቤቱ ተሰገሰጉ ‹‹ ‹‹አረቄ ፋብሪካ ምን እንደሚገጨን ታውቂያለሽ ?›› አለኝ ፣ እረ አላውቅም ‹‹ በየወሩ ሉክ! በየወሩ እ…ስድስት ስድስት ጠርሙስ አረቄ ይገጨናል ፣ እኔ ደግሞ እ…ሀላፊ መሆኔን አስመልክቶ ከአንድ ቮድካ ጋር ዱቅ ይደረግልኛልልልል ፣ አሁን ያዝ ከእግዜር ውሀህ ጋር ችርስ አቦ!›› አለኝ በደስታ ፣ አሁንም እኔ ግን አዘንኩ ፣ ከነበራቸው ቀንድ ያወጣ ሱስ ላይ ጥቅማ ጥቅም ብሎ ይሄንን የመሰለ ሰይጣን ተግባር መፈፀም ፣ በቃ ሰርክ ሳገኛቸው ጓደኞቼን አጭሰው ከስለው ፣ ጠጥተው ሰክረው ፣ ሌሎቹማ ስንቶቹ ቤት ሰርተው ሰርተው ፣ አከራይተው አፈናጠው ምናምን እኚህ የኔዎቹ ፣ ሱሳቸው እንጂ ህልማቸው ላይ መፈናጠጥ አልቻሉም ፣ በቃ ስናወራ ብትሰሙ ህልማቸው ሌላ ፣ መዋያቸው ሌላ ….ፍየል ወዲያ …..ቅዝምዝም….ምናምን ብቻ በቃ …ለነገሩ እኔም ብሆን ህልሜን አልኖርኩም ግን ምንም ቢሆን በጣም በጥቂቱም ቢሆን ከነሱ እምሻለው ፣ ይቺኑ ጥቂት ህልም በአረቄ ምናምን አላጠብኳትም አሁንም አብራኝ አለች፡፡
የዚህኛው ሱስ ደግሞ ለየት ይላል ፣ የዚህን ሱስ እንኳን እኔም ቢይዘኝ የት በደረስኩ ያልኩበት ነበር ፣ የዚህኛው ጓደኛዬ ሱስ ምግብ ነው ታድሎ ነገር ግን ለዚህ አገር አይሆንም ምናምን እሚሉ የደሀ አመለካከቶችና ነቆራዎች ይደርሱታል ፣ ግን በልቶም ያስመሰክራል እኮ ፣ እኔ ፀጉሬን እያሻሸው ስወጣ ትዝ ይለኛል ገና ከህፃንነታችን እሱ ሁዱን እያሸ ነበር ብይ ለመጫወት እምንጠራራው ፣ በቃ የሆነ ሲያድግ እራሱ በደንብ እንዲበላ ይመስላል ፣ ከሌሎች ኢትዮጲያውያን ቤት በተለየ እነሱ ቤት ስለ ምግብ በደንብ ይተረት ነበር ፣ እነ ካንጀት ካዘኑ …….፣ እነ ሆድ ያባውን………፣ እነ ሲበሉ የላኩት ብቻ ምን አለፋቹ በቃ በሆድ ዙሪያ የተነገሩ ሁላ እነሱ ቤት ተፅፈዋል ፣ ሆዳም ሁላ!
እና ይሄ የሆድ አባት የእህል አፈንፋኝ ፣ አድሉ እያሸተተች ሄዳ ሆቴል እንዲቀጠር አደረገችው ፣ በቃ ከምንጩ ተጣደበት ነው ያሉት የሰፈር ሰው ሁላ ፣ ‹‹በስማም እንግዲህ በምግብ ሊጠመቅ ነው በሉኛ ›› አሉ እማማ እንትና አፋቸውን አጣመው ሆ ፣ እሱ ለጎረሰ የሳቸው አፍ ማጣመም እስቲ ምን ይባላል ፣ አይ አበሻ እንደው ፣ አስቂኝ ነገሮች ነን አንዳንዴ!
እና እንደፈረደብኝ ይሄም መጥቶ ስራ ሲቀጠር ነገረኝ ፣ እኔ ይኸው እነሱ ስራ ይቀጠራሉ ፣ ይቀጠራሉ ፣ ሱሰኞቹ እንኳን ስራ አግኝተው እኔ በቃ ይሄው ቁጭ ብዬ እነሱን መምከር ሆኗል ስራዬ ፣ አንድ ቀን ግን የጤነኞችም አምላክ ፣ ለኔም ያሽረኝ ይሆናል፡፡ እና ያው እንዳልኳችሁ የዚህኛው ጥቅማጥቅም ደግሞ በቃ መብላት ነው ‹‹ ቁርስም ፣ ምሳም ፣ እራትም የሚችል ሆቴል አይተህ ታቃለህ? ለነገሩ አንተ እንዴት ታያለህ ፣ የተማርከው መረጃ ምናምን ምግብ በዞረበት እማይዞር ፣ እየውልሽ እኔ የሆዴ አምላክ ፣ ስንት ሺኅ ክትፎ በሚዛቅበት ፣ ስንት ሺኅ በቃ የምግብ አይነት በሚፈተትበት ማህሌት ውስጥ እኑር አረገኝ ፈጣሪ እና ያመጣልኝን እየበላሁ መኖር ነዋ›› አለኝ ፣ እኔ እንዲያ ሲነግረኝ እራሱ ገና ማስታወቂያ ሳይ ውዬ አረፍ ማለቴ ነበር ምሳ እንኳን አልበላሁም ፣ ተመልከቱ እስቲ ታዲያ በይ እና ተበይ ፣ ጭስ እና አጫሽ ፣ መጠጥ እና ጠጪ ሲገናኙ ስራ ለሰሪው አያሰኝም ….ምናለበት እንዲህ ሁላችንንም በምንፈልገው ቦታ ቢቀጥረን ….አይዟችሁ አይቀርም ፣ ግን ሱስን ወዲያ ፣ አስቡት እስቲ የሰው ልጅን ያህል ታላቅ አሳቢና አገናዛቢ ፍጥረት ፣የምን በሆነ ግኡዝ ነገር ፣ሱስ ተይዞ መጠፍነግ ነው ፣ እረ ላሽ!

Wednesday, November 6, 2013

አለቃና ጭፍራ

አለቃና ጭፍራ

ካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

አይ አኛ ቅጥረኞች ፣ አስራ ምናምን አመት ተምረን ዲግሪ ምናምን በጥሰን ስናበቃ ስንት የበጣጠሰ ጭንቅላታችንን ለሆነ ግለሰብ መስሪያ ቤት የ30 ቀን ወያላነት መቅጠራችን ሳያንስ አሁን አሁንማ ጭራሽ ማንነታችንን ሁሉ ነው እኮ ለቅጥረኛነት አሳልፈን የሰጠነው ፣ ይሄን ልል የቻልኩት አለምክኒያት አይደለም፣ ባጠገቤ ብዙ የማውቃቸው ሰዎች ከዱሮ ባሪያ ንግድ ባልተናነሰ ለቀጣሪ ባለሀብታቸው ሲሽቆጠቆጡ አያለሁ፡፡ በቅርብ የማውቀው እና ለወትሮው በራስ መተማመኑ ከፍተኛ የነበረ አንድ ጓደኛየ በቀደም ለት፣ እሱ ቢሮ ሄጄ እያወጋሁ ሳለ፣ የድርጅቱ ባለቤትና የጓደኛየ አለቃ ያው የተለመደ ሱፉን ገጭ አርጎ ፣ በከረባት ታንቆ ፣ ያው የተለመደ የባለሀብትነት ምልክቷን የመኪና ቁልፍ በጁ ይዞ ወዲያና ወዲህ እያቅጨለጨለ ፣ የጓደኛዬን ቢሮ አንኳኳ ፣ እኔ ቀድሜ በመስታወት ውስጥ ተሸግሬ አመጣጡን አይቼ ነበር ፣ ኮራ ቀብረር ማለት ያበዛል ፣ ፊቱን አይተው ደሀ እንደሚንቅ የሚያስታውቅበት ሰው ነው ፣ በሩን አንኳኳ እንጂ እስክንከፍትለት አልጠበቀም እራሱ በርግዶት ገባ ፣ ታዲያ ያኔ የኔው ጉደኛ ጓደኛ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹ ወይኔ ጉዴ ብዙ ሰአት አንኳኩ እንዴ ጌታዬ! ፣ አልሰማዎትም ነበር እኮ ፣ ለምን ያንኳኳሉ ቆይ ፣ ለመሆኑ እስቲ እጣዎት ያንኳኩበት አላመመዎትም ይሆን? ›› ብሎ እጣታቸውን ለጥ ብሎ ማሻሸት ሲጀምር ፣ በቃ ያኔ የት እንዳለሁ አላቅም ፣ የኔ ጓደኛ ስለመሆኑም ተጠራጠርኩ ፣ ኢትዮጲያዊ ስለመሆኑም አሰብኩ ፣ ‹‹እንዲህ አይነት መሽቆጥቆጥ በዘራችን የለም›› ይል ነበር አያቴ ፣ እኔ ግን እምለው እንደውም ‹‹ እንዲህ አይነት መሽቆጥቆጥ ባገራችን የለም›› ነው ፣ እንዲያ ቢሆንማ አበሻ በቅኝ ግዛት በተቀፈደደ ነበር፡፡ አረ ጎበዝ ፣ ከልክ ያለፈ ማጨብጨብስ የሆነ የዱሮ ባሪያ ስታይል ነው!
‹‹ ማነው ደሞ ይሄ ከየት የመጣ ነው?›› አሉ የሱ ጌታ ፣ እ….ብሎ እየተንቀጠቀጠ ጀመረ ‹‹ እ….ጓደኛየ ነው ፣ ሊጠይቀኝ መጥቶ ነው ጌታየ›› አላቸው አይናቸውን እንኳን ቀና ብሎ ሳያይ..‹‹ እንዲህ ነችና ›› ብለው ማጓራት ጀመሩ ‹‹ እና በስራ ሰአት ነው መጥቶ የሚጠይቅህ አንተ?›› ቀጠሉ ‹‹ የኔ ቢሮ ከጓደኛህ ጋር መቀጣጠሪያ ቡና ቤት አረከው አንተ? ››
አልቻልኩም በቃ እንዲህ ሲሉ መስማት ግን አልቻልኩም ልናገር ወሰንኩ ፣ ቢፈልጉ በኔ ሰበብ ያባሩት የእውነት አምላክ ያቅለታል አልኩና ‹‹ ሄይ ሄይ አንዴ ›› ብየ ድንፋታቸውን በማቋረጥ ጀመርኩ ፣ እሱ እኮ እንኳን ሄይ ሄይ ብሎ ሊናገራቸው ቀርቶ ሀይ እንኳን አይላቸውም ፣ ይልቁንም በረጅሙ ፣ ‹‹ እንደምን አደሩ ጌታየ ፣ እርሶን ያኑርልን ፣ እኛን ደግሞ ጠንካራ ሰራተኛ አድርጎ ፣ ድርጅቶን ትርፋማ ያድርግልን ›› በስማም ሎምን አይቀርም ጎበዝ በልክ ነው እንጂ…
እና እኔ በንዴት ንግግሬን ቀጠልኩ ‹‹ እየውሎት ፣ በደንብ ይስሙኝ እሺ ፣ ልጁን እውቀቱን እና ጭንቅላቱን እንጂ የቀጠሩት ፣ ሁለመናውን አሳልፎ የሚሰጥዎት ባሪያዎ እንዲሆን አይደለም ፣ ምናልባት ይሄ አይነት አመለካከት በዱሮ ጊዜ ይሰራ ይሆናል ፣ ያውም ሌሎች አፍሪካ ሀገሮች እንጂ ፣ ኢትዮጲያ ውስጥ I think እርሶ የመጀመሪያው ባላባት ጓደኛዬ ደግሞ የመጀመሪያው ባሪያ ሳትሆኑ አትቀሩም ›› ቀጠልኩ እረ አልበቃኝም ‹‹ እርሶ እንዳሉት ደግሞ ፣ ቡና ቤት መሰለህ እንዴ የኔ ቢሮ ላሉት ፣ እኔ እና እሱ ቡና ቤት ተቃጥረን አናውቅም ›› ብዬ ልቀጥል ስል አቋረጡኝና ‹‹ ምን በምናቹ ትጠጡታላችሁ ፣ ብር ስለሌላቹ ነዋ ፣ ቡና ዝም ተብሎ እንደ ውሀ ተለምኖ እሚጠጣ መሰለህ እንዴ ›› አሉኝ ..ያኔ በጣም ተናደድኩ ፣ በጠዋት እስቲ ከሰው ጌታ ጋር እዚህ ምን እግር ጥሎኝ ነው ….ቀጠልኩ በንዴት ‹‹ ትሰማኛለህ አንተ ሰውዬ›› በጣም ስሌበሳጨው ሳይታወቀኝ ከአንቱታ ወደ አንተ ወረድኩ ፣ ያኔ ጓደኛዬ ምን ውስጥ ይግባ ወይ ዝም በሉ ብሎ መናገር አይችል ፣ ወይ መብቱን አያስከብር ፣ ዝም ብሎ እኔን አይን አይን ያየኛል ፣ ይሄኔ እኮ መቸም ካሁን በኋላ እዚህ ስራ አያስቀጥሉኝም ፣ ይሄ ሰይጣን የሆነ ልጅ በምን ቀን ነው የተዋወኩት ፣ ካባረሩኝ እስቲ የት ልሰራ ነው ፣ እያለ በውስጡ እያሰላሰለ ይሆናል ፣ በራስ መተማመኑን ሰውየው ስለነጠቁት ሌላም ቦታ ቢቀጠር ያው እንደሚሆን ሳስበው እኔም አሳዘነኝ ፣ ግን ሰውየውን ልክ ልክ መንገር አለብኝ ብዬ ቀጠልኩ ፣ እረ እንኳንም አንተ አልኳቸው ፣ ዱሮም ለማይገባቸው ሰው ነው አንቱ ብዬ የጀመርኩት ፣ እዛ ላይ ደግሞ አስቡት እስቲ አንቱ ብሎ መሳደብም ፣ እንደው ለጠብም አይመችም እኮ አንቱታ!
‹‹ እየውልህ ትሰማኛለህ አንተ ሰውዬ ፣ እኔ ጓደኛዬ ትልቅ የተከበረ ቢሮ ውስጥ ነው ፣ ድርጅት ውስጥ ነው እሚሰራው ብዬ ነው የመጣሁት ፣ ደግሞም ማንም ሰው ጓደኛውን እገረ መንገዱን ሲያልፍ እሚሰራበት ቦታ ሄዶ ቢጠይቀው ምንድን ነው ችግሩ ፣ ደግሞ እኮ እየሰራ ሊያዋራኝ ይችላል ፣ ስራው ባፍ እሚታኘክ ነገር አይደለም አይደል? ምን አይነት አገዛዝ ነው ባክህ እምትገዛው ፣ አታፍርም እንዴ በዚህ ዘመን ፣ እንደጊዜው ኑር እንጂ ፣ አንተ ሀብት ቢኖርህ እንደኛ አይነቱን ጭንቅላት ካላገኘህ ብር ብቻውን ምንም አይሰራም ፣ ስለዚህ በምንህም ልትንቀባረር እና ›› ልበለው አልበለው ብዬ ‹‹ ልታናፋ አትችልም እሺ….›› 㙀ልኩጽ በድፍረት ምን ያመጣል ቢያባረው እሱን እንጂ ከኔ ላይ ድርሽ አይልም …..ለጥቂት ደቂቃ ዝምታ ሆነ ፣ ፀጥታ በዚያች ቢሮ ነገሰ ፣ በኋላ ሰውየው ተነፈሱ ‹‹ እ…..ጥሩ ተናጋሪ ነህ ልበል ›› ሲያመሰግኑኝ ግዜ አንቱታቸውን መለስኩላቸው እና ‹‹ ይበሉ›› አልኳቸው ፣ ጭራሽ እኔን አስፈቅደው ማወራት መጀመራቸውን ሲያይ ጓደኛዬ ምን ውስጥ ይግባ በራሱ አፈረ ፣ እ…. ብለው በረጅሙ ተንፍሰው ቀጠሉ ፣ ‹‹ እየውልህ እኔ ማንንም ሰው የመግዛት ፣ እንደ ባሪያም የማየት ልምድ የለኝም ፣ ምንም እንኳን እድሜ ከፍ ቢልም ፣ የዘመኑን አኗኗርና ፍላጎትም ጭምር አውቀዋለሁ u know ፣ ነገር ግን አንዳንድ ግዜ ሰዎችን ወደማይፈልጉትና ፈፅሞም ተመኝተውትና አስበውት ወደ ማያውቁት አለም የሚመሯቸው እራሳቸው ሰዎች ናቸው ፣ አየህ ይሄ ጓደኛህ ዲግሪ ለመያዙም እጠራጠራለሁ ፣ በራሱ ቢተማመን ኑሮ ፣ እራሱን እንደ ባሪያ ባልገበረ እና እኔንም እንደ ጌታ ባልቆጠረ ነበር ፣ ስለዚህ እማላውቀውን ባሪያ ሆኖ እንም ሆኜ እማላውቀውን ጌታ እንድሆን ያደረገኝ እሱ ጭባ ጓደኛህ ነው ፣ አሀሀሀሀሀ ›› ብለው በረጅሙ እኔን እና እሱን እያስተያዩ ሳቁ ፣ ‹‹ እና እኔ ነኝ ወይስ እሱ ጥፋተኛው ጃል? Anyways try to advice him not to act like this ›› ብለውኝ ቢሮውን ጥለው ወጡ ፣ ሰውዬው በጣም ታላቅ ንግግርን ተናግረዋል ፣ እኔ እንኳን ብዙ ግንፍል ግንፍል እያልኩ ለተናገርኩት ፣ ከቁብ ሳይቆጥሩኝ መልስ አልሰጡኝም ፣ ታላቅ ናቸው ፣ በስተት አንተ አልኳው ፣ የንዴት አምላክ ይቅር የበለኝ እንግዲህ….እራሳችንን አሳልፈን ካልሰጠን በቀር ሰዎች እኛን ለመቆጣጠርና ለመግዛት አይፈቅዱም ፣ አኛው በር ከሰጠናቸው ደግሞ ማንም ይሉኝታ አያጠቃውም ፣ ማንም ይረማመድብናል እንጂ ….ስለዚህ ጎበዝ በሚገባው ልክ እንከባበር እንጂ አንሽቆጥቆጥ፡፡

Monday, October 14, 2013

ሀገር ማለት….

ሀገር ማለት….

                                                  በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

ይህ ግዜና ይህ ሰአት፣ ይህ ወቅትና ይህ አመት በጣም ልዩ ነው ፣ ቃል ብቻ እሚገልፀው ሳይሆን አይን አይቶ የመሰከረው እጅግ ውብ ነገር ነው እየታየ ያለው፡፡ እግር ኳሱ ይዞት የመጣው አዲስ ቅኝት አለ፣ አዲስ ውበት አለ፣ ውስጠትን ማንነታችንን የገለፀበት ቋንቋ አለ፡፡ ሰሞነኛ እንዳይሆን እንጂ ይህ ያሁት ነገር፡- 
አገሬ  ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
እያለ እሚቀጥለውን የገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥም አስታወሰኝ፤ ከዚህ ግጥም ስንኝ "ቀለም የሞላበት" እምትለውን እንድዋስ ያስገደደ ሰሞንና ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡ በቃ ይቺ ናት ሀገሬ ብዬ ደግማ ሳትጨልም በካሜራ ቀርጨ እንዳስቀምጥ ያስገደደ ሰሞን፣ ከማላውቀው ከማያውቀኝ ነገር ግን እጅግ ውብ ከሆነ እትዮጲያዊ ጋር በስሜት ያስተቃቀፈ ሰሞን፣ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችን ቋንቋ አንድ ያደረገ ሰሞን፣ እስትንፋስና ደማችንን እንዲሁም ቀለማችንን አንድ ያደረገ ሰሞን መሆኑን ሳስብ ድጋሜ ሌላ ግጥም ትዝ አለኝ፣ ምስጋና ለባለቅኔዎቻችን ይሆንና ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ "ሀገር ማለት የኔ ልጅ" ከሚለው ግጥሙ መሀል ለዚህ ወግ የሚመቸኚን ስንኝ ልዋስና እንዲህ ይላል፡-
ሀገር ማለት የኔ ልጅ 
ሀገር ማለት ቋንቋ ነው በአንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት፤
አማርኛ ኦሮሞኛ  አፋርኛ ቅማንተኛ፤
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ፣ ብለው የማይፈርጁት 
የኔ ልጅ፣
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞውና ሲዳማው  ጉራጌኛሽን ባይሰማ፤
ያልገባው እንዳይመስልሽ  ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስታወት፤
ሲከፋሽ ትሽሽጊበት  ሲደላሽ ትኳኳየዪበት 
እናም ባንደበት ሳንናገረው በገሀድ እንዳየነው፣ በጆሮ ሳንሰማው በህሊናችን እንዳደመጥነው፣ በብሄርብሄረሰብ ሳንገደብ ባንድ ቋንቋ እንዳወራነው፣ ህዝብንና ትውልድን ባንድ ሰንደቅ እንዳስተሳሰረ፣ የሁለንተናችን መስታወት እንደሆነም፣ ስንደሰት በሰንደቅ እንደተሸፋፈንን ሲከፋንም በሰንደቋ መሸሸጋችንን ከዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በላይ፣ ከዚህ ግጥም በላይ እኛ በገሀድ ያየነው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለብሰነው በሰነበትነው አረንጓዴ፣ቢጫ ቀይ ከለር ውስጥ የሀገር ፍቅር ይታይ ነበር፣ ተሰብስበን በቆምንበት ሰአት አንድነትን መናፈቃችን ይታይ ነበር፣ በፈገግታችንንም ይሁን  በሀዘናችን መሀል ፍፁም የሆነ የሀገር ስሜት ይታይ ነበር፣ ለኔ አረንጓዴ ቤጫ ቀዩን ቀለም ስንቀባ ፣ በልባችን ፍፁም የኢትዮጲያዊነትን ፣ የዐንድነትን ደም ፣ የፍቅርን ቃል ኪዳን ፣ የባንዲራን አደራነት ስልጣን የተቀባን ነው የመሰለኝ፣ ለኔ ተቃቅፈን በየጎዳናው አንድ ላይ ባንድ ቀለም ስንሄድ፣ ስንቦርቅና ስንደሰት፣ ስናዝንና ስንከፋ የዋልነው፣ የቀድሞውን ማንነታችንን፣ የአንድነት እትብታችንን ለማደስ ነው፣ ጌዜና ወቅት ያቋረጠውን ፍቅራችንን ለመጠገን ነው እላለው፣ ሺ ውበት፣ ሺ ቋንቋ፣ እልፍ ልዩነቶች በትልቁ አንድ ሆነው የታዩበት፣ የጠፉ ማንነቶች ከየጓዳው የተመዠረጡበትን ቀን ነው እየኖርን ያለነው፡፡
ሰዎች የተከፋፈለ ማንነታቸውን ፣ ጥለት የተቀባ ታሪካቸውን በተለያዩ ምክኒያቶችና ሰበቦች ያድሳሉ፣ ከነዚህም መካከል እንዲህ አይነቱ ብዙሀኑን የሚያሳትፍ ኳስና መሰል ጨዋታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለኔ ለዘጠና ደቂቃ ከሚለጓት ኳስ እና ቡድኑ ከሚያመጣው ውጤት በላይ በኛ በተመልካቹ ላይ የሚያመጣው ታላቅ ሰጋዊ ወመንፈሳዊ ነጥብ አለ፣ ዛሬ እኮ ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ማንን እናሰልፍ ማን ይጫወት የማያውቀው ሰው እንኳን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ስላየ ብቻ ጥቅምት 3ትን ሲጠባበቅ ነበር፣ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ቡድን ስለተባለ ብቻ አንዳች ህመምና ጭንቀትን ሁሉም ዳር እስከዳር ተጨንቋል፣ ዛሬ ይህ ህዝብ እልፍ ቁስሉንና ህማሙን በሰንደቁና በቀለሙ ሸፍኖታል፣ ስንት ሺህ መነጣጠሎችንና መነፋፈቆችን በዚህች ድቡልቡል ኳስ ሰበብ ድል አድርጓል፡፡ በዚህች ኳስ ምክኒያት የተነጣጠለ ትውልድ ተገናኝቷል፣ የተደበቀ ህያው ፍቅር አደባባይ ወጥቷል፡፡ ውበታችንንና አንድነታችንን ያሳየነው እኮ ሜዳ ውስጥ ለናይጀሪያዎቹ ብቻ አይደለም ይልቁንም ከምንምና ከማንም በበለጠ ለራሳችን እና ለእኛው ወገን፣ እንዲህ መፋቀር እየቻልን ለተጣላን፣ እንዲህ አንድ ነበርንን ስሜት ለራሳችን መልክት ያስተላለፍንበት፣ ያገር ፍቅር በግድ እሚነጥቁንን እምቢኝ አሻፈረኝ ያልንበት መድረክ ጭምር እንጂ ለኔ አዲስ አበባ ስቴድየም እግር ኳስ ሜዳ ብቻ ሆኖ አልዋለም፡፡
እንግዲህ ሀገር ማለት እንዲህ ከአይን በላይ ጠልቀው የሚያዩት ከሆነ፣ ከጆርም በላይ የሚያደምጡት ከሆነ፣ ከጥርስም በላይ በውስጥ የሚስቁበት ከሆነ፣ ከቋንቋም በላይ ቋንቋ ያለው ከሆነ እንዲሁ እንደጀመርን ቀደምት ማንነታችንን የምናሳይበትና የምናድስበት ይሁን እላለሁ አሁንም ይቅናሸ ሀገሬ፡፡


Friday, October 4, 2013

የካሌብ ማህሌት: "ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ"

የካሌብ ማህሌት: "ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ": " ምርጥ   የኢትዮጲያ   ልጅ "                                                                                                   ...

"ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ"



"ምርጥ  የኢትዮጲያ  ልጅ"

                                                                                                                                                       በካሌብ  አለማየሁ

የሆነ  ቀን  በሆነ ስሜት ወደ ሆነ የመጠጥ  ቤት  አመራሁ፡ እሁድ ቀን ነው፡ ይህ ቀን ሁል ጊዜ ከሌሎቹ በተለየ  መልኩ  ይረዝምብኛል፡፡ እናም  የረዘመውን  ቀን  እማሳልፈው  በል ሲለኝ መፅሀፍ በማንበብ፣  በል ሲለኝ /ክርስቲያን በመሄድ፣  በል ሲለኝ ኳስ በመጫወት ወይም  ደግሞ ፊልምና ቲያትር በማየት አሳልፋለሁ፡፡ በዚችኛዋ  እለት  ግን በቃ  ቀኑ ይከብዳል ፤ እንደ  መርግ  የከበደ  ቀን ስለሆነብኝ  ትንሽ  ፉት  ብዬ  እራሴን  ከከበደኝ  ነገር  ለማላቀቅ  አሰብኩ፡፡ ከከተማችን  ስር ወደምወዳት  ቦታ  ፒያሳ አቀናሁ፡፡ፒያሳ  ጣይቱ  አጠገብ  ወዳረፈች  ካቲካላ  ደሴት  ጎራ  አልኩ፡፡ ጋሽ  ስብሀት  በአንድ  ወቅት  "ለመሞት ከወሰንክ  መጀመሪያ  ፒያሳ  ሂድ  ምናልባት  ሀሳብክን ልትቀይር  ትችላለህ" ያለው ትዝ አለኝ፡፡ እኔም  ታዲያ  መሞት  ሳስብ  ብቻ  ሳይሆን  መኖር ሳስብም  ወደ  ፒያሳ  አመራለሁ፡፡ ከገባሁበት  መጠጥ  ቤት  ቀዝቃዛ  ቢራ  አዝዤ  መጎንጨት ጀመርኩ፡፡ ቤቱ እዛም፣  እዚህም፣  መሀል  ላይም  እንዳለ  መቀመጫዎቹና  ጠረጴዛዎቹ  በሰውና  በመጠጥ ተሞልተዋል፡፡ ሁሉም ይጠጣሉ፣ ይጮሀሉ፣ ይስቃሉ፣ እያወሩም  ማድመጥ  እንደሚቻል እዚያ ቤት ውስጥ  ነው  ለመጀመሪያ  ጊዜ  ያየሁት፡፡ ሁሉም  እኩል  ያወራሉ፤  መነቃቀፍም  መተቃቀፍም  እኩል  ይከሰታሉ፡፡ አጠገቤ  ሁለት ሽማግሌና  ሁለት ጎልማሳ አራት  ሰዎች  አንድ  ላይ  ተቀምጠው  ይጠጣሉ፡ ሁለተኛ  ቢራዬን አዝዤ  መጠጣት እንደጀመርኩ  ከአራቱ ሰዎች  መሀል  አንዱ  ጎልማሳ  ጣቱን ወደ  እኔ  እየጠቆመ  "ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ  እዩት!"  አላቸው፡፡ ሁሉም  ተሳሳቁ ፍንድቅድቅ  አሉ፡፡ ‘ለነገሩ የሰከረ  ሰው  በማያስቀውም  ይስቅ  የለ’ ብዬ ሀሳቡን   ላጣጥለው  አስቤ  አልሆንልኝ  አለ፡፡ ‘ ቆይ  ለምን ሳቁ ?  እሱ  እንዳለው  ምርጥ  የኢትዬጲያ ልጅ አልመስልም እንዴ ? ስል ለራሴ  ጠየቅሁ፡፡  ምርጥ  የኢትዬጲያ ልጅ ያለኝ ጎልማሳ  አውራ  ጣቱን  ወደ  ላይ  ቀስሮ "ፒስ  ተጫወች!" አለኝ በሴት አጠራር፡፡ እኔም የወጣትነትንና  የስካርን  እንዲሁም   የአራዳን  ባህል  ላለመጣስ ስል እንደሱ አዉራ  ጣቴን  ፉኒን አርጌ  ‘ ፒስ ይመችሽ!’ አልኩት፡፡ሙዚቃው ከድራፍቱና ከውስኪው  እኩል  ይንቆረቆራል፤  ሊጠጣ  የታደመው  ምእመን  ግን  አንዳንዱ  በፈጠነ  ዘፈን ላይ የቤክርስቲያን  ሽብሸባ አስተኔ ይቃጣዋል፡፡ ‘ ዘፈን  ወዲያ፣  ዳንስ ወዲህ’  እሚል  ተረት ለራሴው  ተረትኩና  ሌላ ቢራ እንዲያመጣልኝ  ወዳስተናጋጁ  በትህትና ተመለከትኩ፡፡ ቢራውን ከማዘዜ በፊት ግን አንድ ጠቆር አጠር ያለ ጎልማሳ ሰው አጠገቤ መጥቶ ሰላም አለኝ፤ ይህ ሰው ቅድም ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ ብሎ ሰላም ያለኝ ሰው ነው፡፡ "ኬክዬ፣ ያዕቆቤ፣ ምርጥ የኢትዬጲያ  ልጅ  ችርስ!" ብሎ ከቆመ ባዶ የመጠጫ ጠርሙሴ ጋር የሱን ውስኪ በኩራት አጋጨው፡፡ አይኖቹ እንሶስላ የሞቀ ይመስል በጣም ቀልተዋል፤ ሰውነቱ ግሏል፣ ፊቱ ከገመድ የተሰራ እስኪመስል ጅማቱ ተወጣጥሯል፣ ሲራመድና ሲናገር ግን ትኩስ ቡናም ባፉ የዞረ አይመስልም፤ የፈለገውን ሀሳብ በሚያስገርም ቃና በደንብ ይናገራል፡፡ " ቺርስ በናትህ ፀሎታችን እንዲሰምርልን!" አለኝ፡፡ መቶ ጊዜ ብርጭቆ ማጋጨት ይወዳል፤  እኔ ለራሴ  ‘ኳ!’   ባለ ቁጥር ካሁን አሁን ብርጭቆውን ሰብሮ ሰርፕራይዝ አረገኝ እያልኩ እየተጨነኩ ነው፡፡ ‘የምን ፀሎት ነው ደግሞ የሚሰምርልን’ ስል ጠየቁት፡፡  "እንዴ! ትቀልዳልህ እንዴ ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ፣ የታሰሩት  እንዲፈቱ መፀለይ አለብን እኮ፣ ዛሬ እኮ እኔና አንተ እነሱ ካልተፈቱ ነፃ አይደለንም፤ እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ እስክንድር ነጋ ስለኔና ስላንተ ጥያቄ ነው እኮ ቃሊቲ የገቡት" አለኝ፡፡ ‘ይችን ነው መፍራት!’ አልኩ ለራሴው ይሄ ሰውዬ ሊያውጣጣኝ ነው ወይስ የእውነቱን ለነሱ አዝኖ ነው? ‘አዎ ልክ ነህ ለነሱማ ፀሎት ይገባል! እንዳልል ማን ያውቃል ወያኔ ልኮብኝ ቢሆንስ? እነሱ እንደሆነ መቸም አንዴ CIA ሆነውብናል’ አልኩ ለራሴ በፍርሀት፡፡ ውስጤን ከመቅፅበት ምን ጊዜ እንዳወቀብኝ አላውቅም ብቻ  " ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ ትፈራለህ እንዴ? " ብሎኝ እርፍ አለ፡፡ እውነቱን ነው ለነገሩ ሰው እንዴት ለፀሎት ይፈራል?  በልቦና ለሚካሄድ ነገር ምናልባት ለእስረኞቹ መፀለያችንን የሚለይ ኤክስሬይ ካልገጠሙልን  በስተቀር. . . እስረኞቹ  አሸባሪ ተብለው ስለታሰሩ ምናልባት ለነሱ መፀለይም አሸባሪ ሳያስብል እንደማይቀር የለየው አልመሰለኝም ይህ ጓደኛዬ›. . .  ለነገሩ እሱ ቆርጧል፣ እንኳን ሌላ አሁን እራሱ እምጠጣው እነሱን ለማስፈታት ነው ብሎኛል እነ ርዕዮት አለሙ እስካልተፈቱ ድረስ መጠጣት እንደማያቆም ነግሮኛል፡፡ የሱ መጠጣትና የታሰረ መፈታት ስላልተገናኘልኝ መልሼ ጠይቄው ነበር፡  " እኔ በጠጣው ጊዜ ወያኔ ያስረኛል፣ ሰው ይታዘበኛል፣ ፍርሀት  ብሎ ነገር ከላየ ላይ ይጠፋል፤ እናም ሰርክ ሲያስጨንቀኝ የነበረን የኔና ያንተን  ነውር ህይወት በደንብ እናገረዋለሁ፤  በድፍረት ለሌሎችም  እሰብከዋለሁ፤  ከዛ  የኔ  ጀግንነትና  ምኞት  በሌሎች እንዲሰርፅ አደርጋለሁ፤  እና እልሀለሁ!  ከዛ በኋላ ትግሉም ፀሎቱም ይፏፏማል፤ ለዚህ ነው የምጠጣው ነው የምልህ ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ ቺርስ! " አለኝ  በኩራት፡፡ ከንግግሩ እንደተረዳሁት  ይህ ሰው መስከር ፈልጎ አይደለም፣ ብዙ የሀገርየወገን ጥያቄዎች የኑሮ ሸክሞች ቢያበሳጩት ነው እሚጠጣው፣ የልቡን ይናገርና ይወጣለትም ዘንድ ነው ሰርክ እሚጎነጨው፡፡ ከጎልማሳው ጋር እንዲህ ተመስጨና ሀሳቡን ሀሳብ አድርጌ፣  ስካሩንም ስካር አድርጌ፣ እየተጨዋወትን ሳለ አንዱ አብረውት ሲጠጡ ከነበሩት ሸምገል ያሉ ሰው መጥተው ካልሄድክ እያሉ ይጎትቱት ጀመር፡፡ ሰውየው ግን እጎትታለው ብለው  እራሳቸው ሊወድቁ ነበርና ‘አረ ቀስ እንዳትጥላቸው!’ እሚል ድምፅ ከኔ ወጣ፡፡ ነገር ግን እኔ አዝኜና አክብሬ እንዲህ በመናገሬ የተመለሰልኝ ምላሽ ያስቃልም ያሳቅቃልም፡፡ ሽማግሌው በንቀት አይን ቁልቁል ወደ ተቀመጥቁበት እያዩኝ  " አረ እንዳትጥላቸው! ማንን ነው እሚጥለው በል!? እኔ መኮንንን ነው እሱ እሚጥለኝ?  አታውቅም  50 አለቃ እንደሆንኩ፣ ወይኔ! ይህ ክንድ ስንቱን እንዳረተመ አረ ጠይቅ፣ አዳሜ እንደው ዝም ብሎ እንደፊኛ ቢወጠር ማን እምፈራው መሰለው ፊኛ!! "  ብለው በኔ ሰበብ እኔን ታከው ሌሎች ወፍራም ሰዎችንም ተሳደቡ፡፡  እኔም አሁን ገና መጠጥ ቤት እንዳለሁ ተሰማኝ፤  ወዲያውም ስነ ምግባሮቹ እንዲህ አይነት ንግግር እንደሆኑ ትዝ ሲለኝ  ሳልከፋ በዝምታ አለፍኩት፡፡
በዚያች  ቤት ውስጥ አንዱ ሌላውን  ሰካራም  ሲል ለሰማ,.. እንዴ! ‘ ቆይ ሰካራም  ባዩ እሱ እዙህ  ቁጭ  ብሎ  ማኪያቶ እየጠጣ መሰለው እንዴ?’ ያስብላል፡፡  እዛች ቤት ከተገባ ባይሰከርም  የሰካራምነትን ካባና ስም መጎናፀፍ ግን ግድ ይላል፡፡ እኔ በዚያች በተባረከች ሰንበት ቀን መጠጥ ባያሰክረኝም ሰክሪያለሁ፣ አጠገቤ ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ ሲለኝ የነበረው ጎልማሳ ሰው ሀሳብ አስክሮኛል፣ እሱ ትንሽ የመጠጥ ሞቅታን ብቻ ነበር እሚፈልገው በተቀረ ግን ዱሮውንም በኖሮውና በፖለቲካው ሀሳብ ሞቅ ብሎት ነው የመጣው..የሞቀን ነገር ምን ማሞቅ ያስፈልገዋል! እንዲያውም ትንሽ ፉት ሲል የባሰ ሀሳቡን አጋለው እንጂ፡፡ የጋለ እና የነደደ ሀሳቡን ታዲያ ከኔ ጋር ሲያወራው፣ ሲተነፍሰው የቀለለው መሰለው፣ያገዝኩትም መሰለው፣ አልፎ ተርፎም " የታሰሩት እስኪፈቱ እንፀልያለን በል" አለኝ፡፡ እኔም አልኩ! እንደሱ ትንሽ ፉት ብለን ባይሞቀንም፣ ስለነሱ ለመፀለይ ግን መጠጣትና ሞቅታ ግዴታ አያስፈልገንም፣ወትሮም እኮ ውስጣችንን አብግኖታል፣ ጥንትም ቢሆን የነሱ ጥያቄ ጥያቄያችን ነው፡፡ ዛሬ ስንት ሺህ ህዝብ በኑሮ ምሬት ብቻውን እያወራ እብድ ተብሏል፣ ስንቶቹ እራሳቸውን ለመርሳት በየጫትና መጠጥ ቤት ተደብቀው ይውላሉ፣በቤት ውስጥ እንኳን ስለ ፖለቲካ ለማውራት ስንቱ እናት አባት ልጁን ይጠረጥራል፣ ስንቱ ልጅ እናት አባቱን ይጠረጥራል፣እርስ በራሳችን እንኳን መተማመን አቅቶናል፡፡ ነገር ግን " ያለ ከፋፋይ ጠር የለን፣ያለ አንድነት ተስፋ የለን" እናደለው ሎሬቱ መድሀኒታችን አንድና አንድ ነው እርሱም አንድነት ነው፣ ውህደት ነው፣ ለሀገራዊ ጥያቄ ማንም ሰው በሀገሩ ላይ ሆኖ መፍራት አይጠበቅበትም፣ በሀሳብ እንኳ ለመግባባት እንዴት እንፈራለን? በእርግጥ በዚች ሀገር በነፃነት ማሰብም አሸባሪነት ነው! ይሁንና ይህን ሽንፈት ተቀብሎ  በመኖር የባሰ ውርደት እንጂ መፍትሄ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡
በዚያች እሁድ ምሽት በዚያች መጠጥ ቤት ውስጥ ያለን ነፃነት ከታዘብኩ በኋላ ምናለ የኢትዮጲያ ህዝብ በሙሉ ሰካራም በሆነ ብዬ ከንቱ ምኞት ተመኘሁ፡፡ ይህን እንድል ያስገደደኝ ግን በኔና በናንት ቤት ያላየሁትን፣ በውጭ በየካፌውና በየመንገዱ ያላየሁትን ፍፁም ነፃነት በዚያች ቤት ብቻ ስለተመለከትኩ ነው፡፡ በዚያ ስለ ሁለንተናዊው  ማለትም ስለ ፖለቲካው፣ኢኮኖሚውና ሀይማኖቱ እገሌ ሰማኝና አየኝ ሳይባል ይወራል፣ እገሌ ያስረኛል አይባልም፣ እንደውም ማሰር የሚባል ፅንሰ ሃሳብ በእንደነዚያ አይነት ቤቶች ነውር ነው፣ ፈፅሞም የተከለከለ ነው፣ ማፍታታት ሀሳብን እና መላ አካላትን ማፍታታት ነው የነዚያ አይነት ቀዬ ህጎች፡፡ እናም ለዚህ ነው ፣ ቢጨንቀኝ ነው እኔም ሁላችንም ሰካራም በሆንን ያልኩት...ከነፃነትም በላይ የሆነ ነገር የለምና፡፡ አሁን ይሄን ስል የሰማኝ ግን "አቤት በመጠጥ ቤትም፣ በሰካራምም ይቀናል" ይል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኔ የቀናሁት በድራፍት አጨባበጣቸው፣ በውስኪ አጠጣጣቸው ፣ በጩኸት በፉጨታቸው፣ በወላቃ ጥርሳቸውና በጠማማ ኮፊያቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን በጠማማ ኮፊያቸው ስር በዋለ በዚያች ቅፅበት ብቻ በሚሰማ ቀጥ ባለ የሀሳብ ነፃነት ነው፣ በወላቃ ጥርሳቸው መሀል ሾልካ በወጣች ጥቂት የፖለቲካ የምፀት ሳቅ ነው፣ በጩኸታቸው ስር በሚነበብ የነፃነት ፉጨት ነው የቀናሁት፡፡
የኔና የጎልማሳው የመጠጥ ቤት ጓደኛዬ ወግ ሲቀጥል..."ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ! የታሰሩት ሲፈቱ እኮ ይሄ መንግስት ይገረሰሳል፣ ይሄ መንግስት ሲገረሰስ ደግሞ መብራት አይጠፋም፣ውሀ አይጠፋም፣ ኢንተርኔት አይጠፋም፣ስልክ ኔትወርክ አያስቸግርም፣ ስራ እንደልባችን እናገኛለን፣ ተምረን በግድ ኮብል እስቶን ላይ ብቻ አንቀጠርም ...ሌሎችንም ችግሮች እንዲሁ ስለዚህ መፈታት አለባቸው!" አለኝ የምሬት ቃና ባለው ድምፅ፡፡ በእርግጥ እነ እስክንድር ስለተፈቱ ብቻ ኢሀዲግ ይለቃል ብዬ በየዋህነት እንደሱ ባላስብም ሀሳቦቹ ግን አሳዘኑኝ እንደሀሳቡ ፣እንደፍላጎቱና እንደፍላጎታችን አምላክ ያድርገው ስል በውስጤ ተስማማሁ፡፡ እኔም እንደሱ አልኩ ምርጥ የኢትዮጲያ ልጆች ሆይ! ሁላችሁም ጠጥታችሁና ሰክራችሁ ሳይሆን በጥሞናና በተረጋጋ ስሜት ስለመብታችን እና በተፈጥሮ ስለተሰጠን ነፃነት በፀሎት ብቻ ሳይሆን በተግባር እንታገል፡፡ 'ምርጥ የኢትዮጲያ ልጆች' ደህና ሰንብቱልኝ፡፡