Monday, October 14, 2013

ሀገር ማለት….

ሀገር ማለት….

                                                  በካሌብ(ስንታየሁ) አለማየሁ

ይህ ግዜና ይህ ሰአት፣ ይህ ወቅትና ይህ አመት በጣም ልዩ ነው ፣ ቃል ብቻ እሚገልፀው ሳይሆን አይን አይቶ የመሰከረው እጅግ ውብ ነገር ነው እየታየ ያለው፡፡ እግር ኳሱ ይዞት የመጣው አዲስ ቅኝት አለ፣ አዲስ ውበት አለ፣ ውስጠትን ማንነታችንን የገለፀበት ቋንቋ አለ፡፡ ሰሞነኛ እንዳይሆን እንጂ ይህ ያሁት ነገር፡- 
አገሬ  ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
እያለ እሚቀጥለውን የገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥም አስታወሰኝ፤ ከዚህ ግጥም ስንኝ "ቀለም የሞላበት" እምትለውን እንድዋስ ያስገደደ ሰሞንና ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡ በቃ ይቺ ናት ሀገሬ ብዬ ደግማ ሳትጨልም በካሜራ ቀርጨ እንዳስቀምጥ ያስገደደ ሰሞን፣ ከማላውቀው ከማያውቀኝ ነገር ግን እጅግ ውብ ከሆነ እትዮጲያዊ ጋር በስሜት ያስተቃቀፈ ሰሞን፣ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችን ቋንቋ አንድ ያደረገ ሰሞን፣ እስትንፋስና ደማችንን እንዲሁም ቀለማችንን አንድ ያደረገ ሰሞን መሆኑን ሳስብ ድጋሜ ሌላ ግጥም ትዝ አለኝ፣ ምስጋና ለባለቅኔዎቻችን ይሆንና ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ "ሀገር ማለት የኔ ልጅ" ከሚለው ግጥሙ መሀል ለዚህ ወግ የሚመቸኚን ስንኝ ልዋስና እንዲህ ይላል፡-
ሀገር ማለት የኔ ልጅ 
ሀገር ማለት ቋንቋ ነው በአንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት፤
አማርኛ ኦሮሞኛ  አፋርኛ ቅማንተኛ፤
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ፣ ብለው የማይፈርጁት 
የኔ ልጅ፣
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞውና ሲዳማው  ጉራጌኛሽን ባይሰማ፤
ያልገባው እንዳይመስልሽ  ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስታወት፤
ሲከፋሽ ትሽሽጊበት  ሲደላሽ ትኳኳየዪበት 
እናም ባንደበት ሳንናገረው በገሀድ እንዳየነው፣ በጆሮ ሳንሰማው በህሊናችን እንዳደመጥነው፣ በብሄርብሄረሰብ ሳንገደብ ባንድ ቋንቋ እንዳወራነው፣ ህዝብንና ትውልድን ባንድ ሰንደቅ እንዳስተሳሰረ፣ የሁለንተናችን መስታወት እንደሆነም፣ ስንደሰት በሰንደቅ እንደተሸፋፈንን ሲከፋንም በሰንደቋ መሸሸጋችንን ከዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በላይ፣ ከዚህ ግጥም በላይ እኛ በገሀድ ያየነው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለብሰነው በሰነበትነው አረንጓዴ፣ቢጫ ቀይ ከለር ውስጥ የሀገር ፍቅር ይታይ ነበር፣ ተሰብስበን በቆምንበት ሰአት አንድነትን መናፈቃችን ይታይ ነበር፣ በፈገግታችንንም ይሁን  በሀዘናችን መሀል ፍፁም የሆነ የሀገር ስሜት ይታይ ነበር፣ ለኔ አረንጓዴ ቤጫ ቀዩን ቀለም ስንቀባ ፣ በልባችን ፍፁም የኢትዮጲያዊነትን ፣ የዐንድነትን ደም ፣ የፍቅርን ቃል ኪዳን ፣ የባንዲራን አደራነት ስልጣን የተቀባን ነው የመሰለኝ፣ ለኔ ተቃቅፈን በየጎዳናው አንድ ላይ ባንድ ቀለም ስንሄድ፣ ስንቦርቅና ስንደሰት፣ ስናዝንና ስንከፋ የዋልነው፣ የቀድሞውን ማንነታችንን፣ የአንድነት እትብታችንን ለማደስ ነው፣ ጌዜና ወቅት ያቋረጠውን ፍቅራችንን ለመጠገን ነው እላለው፣ ሺ ውበት፣ ሺ ቋንቋ፣ እልፍ ልዩነቶች በትልቁ አንድ ሆነው የታዩበት፣ የጠፉ ማንነቶች ከየጓዳው የተመዠረጡበትን ቀን ነው እየኖርን ያለነው፡፡
ሰዎች የተከፋፈለ ማንነታቸውን ፣ ጥለት የተቀባ ታሪካቸውን በተለያዩ ምክኒያቶችና ሰበቦች ያድሳሉ፣ ከነዚህም መካከል እንዲህ አይነቱ ብዙሀኑን የሚያሳትፍ ኳስና መሰል ጨዋታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለኔ ለዘጠና ደቂቃ ከሚለጓት ኳስ እና ቡድኑ ከሚያመጣው ውጤት በላይ በኛ በተመልካቹ ላይ የሚያመጣው ታላቅ ሰጋዊ ወመንፈሳዊ ነጥብ አለ፣ ዛሬ እኮ ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ማንን እናሰልፍ ማን ይጫወት የማያውቀው ሰው እንኳን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ስላየ ብቻ ጥቅምት 3ትን ሲጠባበቅ ነበር፣ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ቡድን ስለተባለ ብቻ አንዳች ህመምና ጭንቀትን ሁሉም ዳር እስከዳር ተጨንቋል፣ ዛሬ ይህ ህዝብ እልፍ ቁስሉንና ህማሙን በሰንደቁና በቀለሙ ሸፍኖታል፣ ስንት ሺህ መነጣጠሎችንና መነፋፈቆችን በዚህች ድቡልቡል ኳስ ሰበብ ድል አድርጓል፡፡ በዚህች ኳስ ምክኒያት የተነጣጠለ ትውልድ ተገናኝቷል፣ የተደበቀ ህያው ፍቅር አደባባይ ወጥቷል፡፡ ውበታችንንና አንድነታችንን ያሳየነው እኮ ሜዳ ውስጥ ለናይጀሪያዎቹ ብቻ አይደለም ይልቁንም ከምንምና ከማንም በበለጠ ለራሳችን እና ለእኛው ወገን፣ እንዲህ መፋቀር እየቻልን ለተጣላን፣ እንዲህ አንድ ነበርንን ስሜት ለራሳችን መልክት ያስተላለፍንበት፣ ያገር ፍቅር በግድ እሚነጥቁንን እምቢኝ አሻፈረኝ ያልንበት መድረክ ጭምር እንጂ ለኔ አዲስ አበባ ስቴድየም እግር ኳስ ሜዳ ብቻ ሆኖ አልዋለም፡፡
እንግዲህ ሀገር ማለት እንዲህ ከአይን በላይ ጠልቀው የሚያዩት ከሆነ፣ ከጆርም በላይ የሚያደምጡት ከሆነ፣ ከጥርስም በላይ በውስጥ የሚስቁበት ከሆነ፣ ከቋንቋም በላይ ቋንቋ ያለው ከሆነ እንዲሁ እንደጀመርን ቀደምት ማንነታችንን የምናሳይበትና የምናድስበት ይሁን እላለሁ አሁንም ይቅናሸ ሀገሬ፡፡


Friday, October 4, 2013

የካሌብ ማህሌት: "ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ"

የካሌብ ማህሌት: "ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ": " ምርጥ   የኢትዮጲያ   ልጅ "                                                                                                   ...

"ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ"



"ምርጥ  የኢትዮጲያ  ልጅ"

                                                                                                                                                       በካሌብ  አለማየሁ

የሆነ  ቀን  በሆነ ስሜት ወደ ሆነ የመጠጥ  ቤት  አመራሁ፡ እሁድ ቀን ነው፡ ይህ ቀን ሁል ጊዜ ከሌሎቹ በተለየ  መልኩ  ይረዝምብኛል፡፡ እናም  የረዘመውን  ቀን  እማሳልፈው  በል ሲለኝ መፅሀፍ በማንበብ፣  በል ሲለኝ /ክርስቲያን በመሄድ፣  በል ሲለኝ ኳስ በመጫወት ወይም  ደግሞ ፊልምና ቲያትር በማየት አሳልፋለሁ፡፡ በዚችኛዋ  እለት  ግን በቃ  ቀኑ ይከብዳል ፤ እንደ  መርግ  የከበደ  ቀን ስለሆነብኝ  ትንሽ  ፉት  ብዬ  እራሴን  ከከበደኝ  ነገር  ለማላቀቅ  አሰብኩ፡፡ ከከተማችን  ስር ወደምወዳት  ቦታ  ፒያሳ አቀናሁ፡፡ፒያሳ  ጣይቱ  አጠገብ  ወዳረፈች  ካቲካላ  ደሴት  ጎራ  አልኩ፡፡ ጋሽ  ስብሀት  በአንድ  ወቅት  "ለመሞት ከወሰንክ  መጀመሪያ  ፒያሳ  ሂድ  ምናልባት  ሀሳብክን ልትቀይር  ትችላለህ" ያለው ትዝ አለኝ፡፡ እኔም  ታዲያ  መሞት  ሳስብ  ብቻ  ሳይሆን  መኖር ሳስብም  ወደ  ፒያሳ  አመራለሁ፡፡ ከገባሁበት  መጠጥ  ቤት  ቀዝቃዛ  ቢራ  አዝዤ  መጎንጨት ጀመርኩ፡፡ ቤቱ እዛም፣  እዚህም፣  መሀል  ላይም  እንዳለ  መቀመጫዎቹና  ጠረጴዛዎቹ  በሰውና  በመጠጥ ተሞልተዋል፡፡ ሁሉም ይጠጣሉ፣ ይጮሀሉ፣ ይስቃሉ፣ እያወሩም  ማድመጥ  እንደሚቻል እዚያ ቤት ውስጥ  ነው  ለመጀመሪያ  ጊዜ  ያየሁት፡፡ ሁሉም  እኩል  ያወራሉ፤  መነቃቀፍም  መተቃቀፍም  እኩል  ይከሰታሉ፡፡ አጠገቤ  ሁለት ሽማግሌና  ሁለት ጎልማሳ አራት  ሰዎች  አንድ  ላይ  ተቀምጠው  ይጠጣሉ፡ ሁለተኛ  ቢራዬን አዝዤ  መጠጣት እንደጀመርኩ  ከአራቱ ሰዎች  መሀል  አንዱ  ጎልማሳ  ጣቱን ወደ  እኔ  እየጠቆመ  "ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ  እዩት!"  አላቸው፡፡ ሁሉም  ተሳሳቁ ፍንድቅድቅ  አሉ፡፡ ‘ለነገሩ የሰከረ  ሰው  በማያስቀውም  ይስቅ  የለ’ ብዬ ሀሳቡን   ላጣጥለው  አስቤ  አልሆንልኝ  አለ፡፡ ‘ ቆይ  ለምን ሳቁ ?  እሱ  እንዳለው  ምርጥ  የኢትዬጲያ ልጅ አልመስልም እንዴ ? ስል ለራሴ  ጠየቅሁ፡፡  ምርጥ  የኢትዬጲያ ልጅ ያለኝ ጎልማሳ  አውራ  ጣቱን  ወደ  ላይ  ቀስሮ "ፒስ  ተጫወች!" አለኝ በሴት አጠራር፡፡ እኔም የወጣትነትንና  የስካርን  እንዲሁም   የአራዳን  ባህል  ላለመጣስ ስል እንደሱ አዉራ  ጣቴን  ፉኒን አርጌ  ‘ ፒስ ይመችሽ!’ አልኩት፡፡ሙዚቃው ከድራፍቱና ከውስኪው  እኩል  ይንቆረቆራል፤  ሊጠጣ  የታደመው  ምእመን  ግን  አንዳንዱ  በፈጠነ  ዘፈን ላይ የቤክርስቲያን  ሽብሸባ አስተኔ ይቃጣዋል፡፡ ‘ ዘፈን  ወዲያ፣  ዳንስ ወዲህ’  እሚል  ተረት ለራሴው  ተረትኩና  ሌላ ቢራ እንዲያመጣልኝ  ወዳስተናጋጁ  በትህትና ተመለከትኩ፡፡ ቢራውን ከማዘዜ በፊት ግን አንድ ጠቆር አጠር ያለ ጎልማሳ ሰው አጠገቤ መጥቶ ሰላም አለኝ፤ ይህ ሰው ቅድም ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ ብሎ ሰላም ያለኝ ሰው ነው፡፡ "ኬክዬ፣ ያዕቆቤ፣ ምርጥ የኢትዬጲያ  ልጅ  ችርስ!" ብሎ ከቆመ ባዶ የመጠጫ ጠርሙሴ ጋር የሱን ውስኪ በኩራት አጋጨው፡፡ አይኖቹ እንሶስላ የሞቀ ይመስል በጣም ቀልተዋል፤ ሰውነቱ ግሏል፣ ፊቱ ከገመድ የተሰራ እስኪመስል ጅማቱ ተወጣጥሯል፣ ሲራመድና ሲናገር ግን ትኩስ ቡናም ባፉ የዞረ አይመስልም፤ የፈለገውን ሀሳብ በሚያስገርም ቃና በደንብ ይናገራል፡፡ " ቺርስ በናትህ ፀሎታችን እንዲሰምርልን!" አለኝ፡፡ መቶ ጊዜ ብርጭቆ ማጋጨት ይወዳል፤  እኔ ለራሴ  ‘ኳ!’   ባለ ቁጥር ካሁን አሁን ብርጭቆውን ሰብሮ ሰርፕራይዝ አረገኝ እያልኩ እየተጨነኩ ነው፡፡ ‘የምን ፀሎት ነው ደግሞ የሚሰምርልን’ ስል ጠየቁት፡፡  "እንዴ! ትቀልዳልህ እንዴ ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ፣ የታሰሩት  እንዲፈቱ መፀለይ አለብን እኮ፣ ዛሬ እኮ እኔና አንተ እነሱ ካልተፈቱ ነፃ አይደለንም፤ እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ እስክንድር ነጋ ስለኔና ስላንተ ጥያቄ ነው እኮ ቃሊቲ የገቡት" አለኝ፡፡ ‘ይችን ነው መፍራት!’ አልኩ ለራሴው ይሄ ሰውዬ ሊያውጣጣኝ ነው ወይስ የእውነቱን ለነሱ አዝኖ ነው? ‘አዎ ልክ ነህ ለነሱማ ፀሎት ይገባል! እንዳልል ማን ያውቃል ወያኔ ልኮብኝ ቢሆንስ? እነሱ እንደሆነ መቸም አንዴ CIA ሆነውብናል’ አልኩ ለራሴ በፍርሀት፡፡ ውስጤን ከመቅፅበት ምን ጊዜ እንዳወቀብኝ አላውቅም ብቻ  " ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ ትፈራለህ እንዴ? " ብሎኝ እርፍ አለ፡፡ እውነቱን ነው ለነገሩ ሰው እንዴት ለፀሎት ይፈራል?  በልቦና ለሚካሄድ ነገር ምናልባት ለእስረኞቹ መፀለያችንን የሚለይ ኤክስሬይ ካልገጠሙልን  በስተቀር. . . እስረኞቹ  አሸባሪ ተብለው ስለታሰሩ ምናልባት ለነሱ መፀለይም አሸባሪ ሳያስብል እንደማይቀር የለየው አልመሰለኝም ይህ ጓደኛዬ›. . .  ለነገሩ እሱ ቆርጧል፣ እንኳን ሌላ አሁን እራሱ እምጠጣው እነሱን ለማስፈታት ነው ብሎኛል እነ ርዕዮት አለሙ እስካልተፈቱ ድረስ መጠጣት እንደማያቆም ነግሮኛል፡፡ የሱ መጠጣትና የታሰረ መፈታት ስላልተገናኘልኝ መልሼ ጠይቄው ነበር፡  " እኔ በጠጣው ጊዜ ወያኔ ያስረኛል፣ ሰው ይታዘበኛል፣ ፍርሀት  ብሎ ነገር ከላየ ላይ ይጠፋል፤ እናም ሰርክ ሲያስጨንቀኝ የነበረን የኔና ያንተን  ነውር ህይወት በደንብ እናገረዋለሁ፤  በድፍረት ለሌሎችም  እሰብከዋለሁ፤  ከዛ  የኔ  ጀግንነትና  ምኞት  በሌሎች እንዲሰርፅ አደርጋለሁ፤  እና እልሀለሁ!  ከዛ በኋላ ትግሉም ፀሎቱም ይፏፏማል፤ ለዚህ ነው የምጠጣው ነው የምልህ ምርጥ የኢትዬጲያ ልጅ ቺርስ! " አለኝ  በኩራት፡፡ ከንግግሩ እንደተረዳሁት  ይህ ሰው መስከር ፈልጎ አይደለም፣ ብዙ የሀገርየወገን ጥያቄዎች የኑሮ ሸክሞች ቢያበሳጩት ነው እሚጠጣው፣ የልቡን ይናገርና ይወጣለትም ዘንድ ነው ሰርክ እሚጎነጨው፡፡ ከጎልማሳው ጋር እንዲህ ተመስጨና ሀሳቡን ሀሳብ አድርጌ፣  ስካሩንም ስካር አድርጌ፣ እየተጨዋወትን ሳለ አንዱ አብረውት ሲጠጡ ከነበሩት ሸምገል ያሉ ሰው መጥተው ካልሄድክ እያሉ ይጎትቱት ጀመር፡፡ ሰውየው ግን እጎትታለው ብለው  እራሳቸው ሊወድቁ ነበርና ‘አረ ቀስ እንዳትጥላቸው!’ እሚል ድምፅ ከኔ ወጣ፡፡ ነገር ግን እኔ አዝኜና አክብሬ እንዲህ በመናገሬ የተመለሰልኝ ምላሽ ያስቃልም ያሳቅቃልም፡፡ ሽማግሌው በንቀት አይን ቁልቁል ወደ ተቀመጥቁበት እያዩኝ  " አረ እንዳትጥላቸው! ማንን ነው እሚጥለው በል!? እኔ መኮንንን ነው እሱ እሚጥለኝ?  አታውቅም  50 አለቃ እንደሆንኩ፣ ወይኔ! ይህ ክንድ ስንቱን እንዳረተመ አረ ጠይቅ፣ አዳሜ እንደው ዝም ብሎ እንደፊኛ ቢወጠር ማን እምፈራው መሰለው ፊኛ!! "  ብለው በኔ ሰበብ እኔን ታከው ሌሎች ወፍራም ሰዎችንም ተሳደቡ፡፡  እኔም አሁን ገና መጠጥ ቤት እንዳለሁ ተሰማኝ፤  ወዲያውም ስነ ምግባሮቹ እንዲህ አይነት ንግግር እንደሆኑ ትዝ ሲለኝ  ሳልከፋ በዝምታ አለፍኩት፡፡
በዚያች  ቤት ውስጥ አንዱ ሌላውን  ሰካራም  ሲል ለሰማ,.. እንዴ! ‘ ቆይ ሰካራም  ባዩ እሱ እዙህ  ቁጭ  ብሎ  ማኪያቶ እየጠጣ መሰለው እንዴ?’ ያስብላል፡፡  እዛች ቤት ከተገባ ባይሰከርም  የሰካራምነትን ካባና ስም መጎናፀፍ ግን ግድ ይላል፡፡ እኔ በዚያች በተባረከች ሰንበት ቀን መጠጥ ባያሰክረኝም ሰክሪያለሁ፣ አጠገቤ ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ ሲለኝ የነበረው ጎልማሳ ሰው ሀሳብ አስክሮኛል፣ እሱ ትንሽ የመጠጥ ሞቅታን ብቻ ነበር እሚፈልገው በተቀረ ግን ዱሮውንም በኖሮውና በፖለቲካው ሀሳብ ሞቅ ብሎት ነው የመጣው..የሞቀን ነገር ምን ማሞቅ ያስፈልገዋል! እንዲያውም ትንሽ ፉት ሲል የባሰ ሀሳቡን አጋለው እንጂ፡፡ የጋለ እና የነደደ ሀሳቡን ታዲያ ከኔ ጋር ሲያወራው፣ ሲተነፍሰው የቀለለው መሰለው፣ያገዝኩትም መሰለው፣ አልፎ ተርፎም " የታሰሩት እስኪፈቱ እንፀልያለን በል" አለኝ፡፡ እኔም አልኩ! እንደሱ ትንሽ ፉት ብለን ባይሞቀንም፣ ስለነሱ ለመፀለይ ግን መጠጣትና ሞቅታ ግዴታ አያስፈልገንም፣ወትሮም እኮ ውስጣችንን አብግኖታል፣ ጥንትም ቢሆን የነሱ ጥያቄ ጥያቄያችን ነው፡፡ ዛሬ ስንት ሺህ ህዝብ በኑሮ ምሬት ብቻውን እያወራ እብድ ተብሏል፣ ስንቶቹ እራሳቸውን ለመርሳት በየጫትና መጠጥ ቤት ተደብቀው ይውላሉ፣በቤት ውስጥ እንኳን ስለ ፖለቲካ ለማውራት ስንቱ እናት አባት ልጁን ይጠረጥራል፣ ስንቱ ልጅ እናት አባቱን ይጠረጥራል፣እርስ በራሳችን እንኳን መተማመን አቅቶናል፡፡ ነገር ግን " ያለ ከፋፋይ ጠር የለን፣ያለ አንድነት ተስፋ የለን" እናደለው ሎሬቱ መድሀኒታችን አንድና አንድ ነው እርሱም አንድነት ነው፣ ውህደት ነው፣ ለሀገራዊ ጥያቄ ማንም ሰው በሀገሩ ላይ ሆኖ መፍራት አይጠበቅበትም፣ በሀሳብ እንኳ ለመግባባት እንዴት እንፈራለን? በእርግጥ በዚች ሀገር በነፃነት ማሰብም አሸባሪነት ነው! ይሁንና ይህን ሽንፈት ተቀብሎ  በመኖር የባሰ ውርደት እንጂ መፍትሄ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡
በዚያች እሁድ ምሽት በዚያች መጠጥ ቤት ውስጥ ያለን ነፃነት ከታዘብኩ በኋላ ምናለ የኢትዮጲያ ህዝብ በሙሉ ሰካራም በሆነ ብዬ ከንቱ ምኞት ተመኘሁ፡፡ ይህን እንድል ያስገደደኝ ግን በኔና በናንት ቤት ያላየሁትን፣ በውጭ በየካፌውና በየመንገዱ ያላየሁትን ፍፁም ነፃነት በዚያች ቤት ብቻ ስለተመለከትኩ ነው፡፡ በዚያ ስለ ሁለንተናዊው  ማለትም ስለ ፖለቲካው፣ኢኮኖሚውና ሀይማኖቱ እገሌ ሰማኝና አየኝ ሳይባል ይወራል፣ እገሌ ያስረኛል አይባልም፣ እንደውም ማሰር የሚባል ፅንሰ ሃሳብ በእንደነዚያ አይነት ቤቶች ነውር ነው፣ ፈፅሞም የተከለከለ ነው፣ ማፍታታት ሀሳብን እና መላ አካላትን ማፍታታት ነው የነዚያ አይነት ቀዬ ህጎች፡፡ እናም ለዚህ ነው ፣ ቢጨንቀኝ ነው እኔም ሁላችንም ሰካራም በሆንን ያልኩት...ከነፃነትም በላይ የሆነ ነገር የለምና፡፡ አሁን ይሄን ስል የሰማኝ ግን "አቤት በመጠጥ ቤትም፣ በሰካራምም ይቀናል" ይል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኔ የቀናሁት በድራፍት አጨባበጣቸው፣ በውስኪ አጠጣጣቸው ፣ በጩኸት በፉጨታቸው፣ በወላቃ ጥርሳቸውና በጠማማ ኮፊያቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን በጠማማ ኮፊያቸው ስር በዋለ በዚያች ቅፅበት ብቻ በሚሰማ ቀጥ ባለ የሀሳብ ነፃነት ነው፣ በወላቃ ጥርሳቸው መሀል ሾልካ በወጣች ጥቂት የፖለቲካ የምፀት ሳቅ ነው፣ በጩኸታቸው ስር በሚነበብ የነፃነት ፉጨት ነው የቀናሁት፡፡
የኔና የጎልማሳው የመጠጥ ቤት ጓደኛዬ ወግ ሲቀጥል..."ምርጥ የኢትዮጲያ ልጅ! የታሰሩት ሲፈቱ እኮ ይሄ መንግስት ይገረሰሳል፣ ይሄ መንግስት ሲገረሰስ ደግሞ መብራት አይጠፋም፣ውሀ አይጠፋም፣ ኢንተርኔት አይጠፋም፣ስልክ ኔትወርክ አያስቸግርም፣ ስራ እንደልባችን እናገኛለን፣ ተምረን በግድ ኮብል እስቶን ላይ ብቻ አንቀጠርም ...ሌሎችንም ችግሮች እንዲሁ ስለዚህ መፈታት አለባቸው!" አለኝ የምሬት ቃና ባለው ድምፅ፡፡ በእርግጥ እነ እስክንድር ስለተፈቱ ብቻ ኢሀዲግ ይለቃል ብዬ በየዋህነት እንደሱ ባላስብም ሀሳቦቹ ግን አሳዘኑኝ እንደሀሳቡ ፣እንደፍላጎቱና እንደፍላጎታችን አምላክ ያድርገው ስል በውስጤ ተስማማሁ፡፡ እኔም እንደሱ አልኩ ምርጥ የኢትዮጲያ ልጆች ሆይ! ሁላችሁም ጠጥታችሁና ሰክራችሁ ሳይሆን በጥሞናና በተረጋጋ ስሜት ስለመብታችን እና በተፈጥሮ ስለተሰጠን ነፃነት በፀሎት ብቻ ሳይሆን በተግባር እንታገል፡፡ 'ምርጥ የኢትዮጲያ ልጆች' ደህና ሰንብቱልኝ፡፡