በስንታየሁ (ካሌብ)
አለማየሁ
ትናትና ወደ ብሄራዊ
አካባቢ ስሄድ….ብሄራዊ ባንክ ፣ ክቡ ባንክ ወይም ወርቃማው ባንክ እየተባለ የሚጠራው ባንክ ፊት ለፊት ስደርስ የሆነ ነገር አይኔን
ያዝ አደረገው….ባንኩ ፊት ለፊት የተሰቀሉ ሁለት ባንዲራዎች አሉ….አንዱ የራሱ የባንኩ ሰማያዊ አስተኔ ባንዲራ ነው….አንዱ ግን
የኢትዮጲያ ባለኮከቡ (ድንቄም ባለኮከብ!) ባንዲራ ነው፡፡……
እዛ አካባቢ ያለው ነፋስ
መቸም አይደለም በገመድ የተንጠለጠለችን ባንዲራ በሰው ገላ ላይ ያለን ልብስ ለማውለቅ ይፈታተናል…..ያች የኢትዮጲያ ባንዲራ ግን
ወይ ንቅንቅ እቴ አንገቷን ደፍታ (አንገት አላት ግን?) እንደ ጨርቅ ለወጉ እንኳን በነፋስ ወዲያና ወዲህ ሳትንቀሳቀስ ….ደሞ
ጨርቅ አልክ በሉና አሸባሪ በሉኝ አሉ…ባንዲራ የትኛውም ሀገር እስከዛሬ እሚሰራው ከጨርቅ ነው…የድንጋይ ወይንም የብረት ባንዲራ
አይቼ አላውቅም….ነገር ግን ጨርቅነቱን ይጥል ዘንድ ከተራ ቁራጭ እራፊነት ይድን ዘንድ ደማችንን ፣ ወኔያችንን ፣ ራዕያችንንና
ብልፅግናችንን ጠቅልለንበታል ከዚህ አንፃር ነው እንግዲህ ባንዲራ ከጨርቅነት የሚያመልጠው፡፡
እናም ያች የጦቢያ ባንዲራ
ነፋስ ባጠገቧ ሲያልፍ ባላየ ላሽ አላለችላችሁም….ባንዲራ በመርገብገብ ብዛት የሆነ አስፈሪ ሞገድ ይፈጥር ነበረ እኮ!! ወይኔ ነፋስ
ባልጠፋበት ሀገር በባንዲራም እስቲ የነ ነበረ ሀገር ልንባል ነው!!.....እረ ምን አለመውለብለብ ብቻ መልኳ እራሱ ጠፍቶ ከወርቃማ
ባንክ ፊት ለፊት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ እሚሉት ከለር ምን ይሰራል የተባለ ይመስል…..ከአቧራው ብዛት የተነሳ ይመስለኛል እንደ አይጥማ
አይነት ከለርም ተጎናፅፋለች!.......ያች የሀገር ምልክት ፣ ያች ጀግኖች የተዋደቁላት ገለመሌ ብለን እምንለፍፍላት ጨርቃችን
እጅጉን ተበሳቁላለች…….
በቃ ሳያት አንጀቴ ልውስ
አለ..ሆዴ ተሸበረ….አንድ እማውቃት ምስኪን ሴት ተበድላ መንገድ ዳር አፈር ጎርሳ አፈር ልሳ ያየኋት ያህልም አዘንኩ…..እንባም
ተናነቀኝ መንገድ ላይ ተገትሬ ቀረሁ…
ምን ተበድላ ይሆን ስል
አሰብኩ…..ባንዲራ ይበደላል እንዴ ይለኛል ሌላኛው እኔ…..ቀላል ይበደላል….ከራሴው ጋር ጭቅጭቅ…ንትርክ ገጠምኩ…
ባንዲራ ለካ ያኮርፋል…..ካከረፈ
ደሞ አውሎ ነፋስም ምንም አያርገበግበውም….ሰው ትንሽ በነፋስ አይነቃነቅም ይቅርታ ሰው አልኩ እንዴ….ለነገሩ ባንዲራ ሰው ማለት
እኮ ነው ያውም ግብዳ ሰው…. ሶስት አይነት ቀለም የተቀባ ሀገርን የወከለ በነፋስ ተርገብጋቢ ሰው …..
ይሄ አካል ነው እንግዲህ
የተሰቀለበት ብረት ላይ ስእል መስሎ ፣ ክንፉን የተመታ አሞራ የተገነጠለ ክንፉን ትቶት ሄዶ…ተንጠልጥሎ የቀረ ግዑዝ አካል መስሎ
ያየሁት…..
ግን ባንዲራ ለምን አኮረፈ
አንልም?…..ይመስለኛል ወክለኸናል ያልነው ህዝብ ስንዋሽ ፣ ስናጭበረብር ፣ ሀገር ስንክድ (ያው የሰሞኑን ኢሊኮፍተር ምሳሌ መጥቀስ
ይቻላል ) ፣ ሙስና ስናረግዝ ስንወልድ ኮትኩተን ስናሳድግ ፣ ጀግንነት ከደጃችን አይደለም ከውስጣችን ሲመክን ፣ አንዴ የኢሊሙናቴ
አንዴ የአንበሳ ምናምን እየሳልን የስእል ደብተር ስናረገው……በነዚህና በሌሎች ባልተጠቀሱ እልፍ አእላፍ ምክኒያቶች ባንዲራው ያኮረፈ
ይመስለኛል፡፡
እኔ እግር ጥሎኝ አንዱን
ባንዲራ አየሁ…እስቲ በየትምህርት ቤታችሁ በየመስሪያ ቤታችሁ በየሆቴሉ የተሰቀሉትን ልብ እንበል ጎበዝ እየተርገበገቡ ይሆን ወይስ
ሁሉም ተማክረው አምፀዋል!?.......ለነገሩ የቤተ መንግስቷ ከተርገበገበች ሀገር ለመወከል ትበቃለች መሰለኝ!!
No comments:
Post a Comment