………………..
በስንታየሁ(ካሌብ) አለማየሁ
ስለ ኳስ ሳስብ ሁሌ
አያቴና የሀይስኩል ስፓርት አስተማሪዬ የነበረው ጋሽ አቤ (ውይ አሁን እንኳን አንቱ ልበል የነበሩት) ትዝ ይሉኛል፡፡
‹‹ኳስ ይሉት እቃ የማንም
መላገጫና እግር ማንሻ አለመታደል ማለት ኳስ ሁኖ መፈጠር ነው›› ይል ነበር አያቴ…..እኔ ታዲያ ቀበል አድርጌ እዲያ አያቴ ደሞ
እሷን እግዜር አልፈጠራት እራሱ አውሬው የሰው ልጅ ነው እንጂ ፣ አውሬነቱን እሚገልፅበት ዝም ብሎ እሚፈነጭበትን መንገድ ሲፈልግ
ነው ኳስን የፈጠራት አለመታደልስ ከጋሽ አቤ ጋር መጫወት፡፡
አቤት ጋሽ አቤ ማለት እኮ በቃ ሲያስተምር እያንዳንዱ የተማሪው አይን ላይ አፍጥጦ ነው
፣ ለነገሩ ማፍጠጡ እንኳን ደግ አረገ ስንት እሚያንቀላፋ ተማሪ ባለበት ፣ ስንት ሱሰኛ ተማሪ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ እያፋሸገ ክላሱን
ፓርላማ ለሚያስመስልበት ትውልድ ጋሽ አቤ ማፍጠጥ አይደለም እነዛን እሚተኙ አይኖች እየዞረ ቢቆነጥጣቸውም አላዝን፡፡ እና ጋሽ አቤ
ክፍል ውስጥ ሲያስተምር አይናችን ላይ መውጣት ነው እሚቀረው ፣ ድንገት ደግሞ መንገድ ላይ አግኝቶህ እሱ እያዋራህ እሱ የጀመረውን
ወሬ ሳይጨርስ ‹‹አዎ ጋሼ…››ምናምን ብሎ እቀጥላለሁ ማለት አለቀለህ ፣ ‹‹ይሄ ክፉ ልጅ ወሬዬን አቋርጦ የሚያወራ ፣ ይሄ እርጉም
ልጅ አሳዳጊ የረገመው እስቲ የት ሊሄድ ነው፣ ሰፈር ድንጋይ ማሞቅ
ነው ስራው ምን አስቸኮለው ቢያደምጠኝ ፣ እሱ ሰው ያስጨርሳል መሰላቹ…›› በቃ ላገር ላገኘው ሰው ያወራል ፣ ስለዛ ልጅ በተነሳ
ቁጥር በቃ ስሙን ነው እሚያጠፋው፡ ጋሽ አቤ እያወራ ድንገት ቢያስነጥሰው እንኳን ‹‹ይማርህ ጋሼ›› ማለት አይቻልም ‹‹ምናገባህ
አንተ ነህ እንዲምረኝ እምታዘው ፣ ምናለበት እስቲ ዝም ብትል…ውይ ውይ ውይ የወሬ ሱስ›› ይልሀል የራሱ በየመንገዱ ሰው 1 ሰአት
ገትሮ ማዋራቱ አይታወቀውም፡ ሰው መቸም የራሱ ጉድ አይታወቀውም ሲባል የገባኝ ያኔ ነው ፡፡
በነገራችን ላይ ጋሽ አቤ የስፖርት መምህራችን ብቻ አልነበርም
አማርኛ የትምህርት አይነትም ያስተምረን ነበር፡፡ ታዲያ ብዙ ጊዜ ትምህርት ቤት ውስጥ ተሰሚነት ስለነበረው ፣ ‹‹እኔ በመውጣት
በመግባት እንደሌላው አስተማሪ አልመላለስም ሁለቱንም ፔረዶች መደዳውን ወይንም ተከታታይ ሰአት ላይ አርጉልኝ›› ብሎ የትምህርት
ቤቱን ዳይሬክተር በማመልክቻ በመጠየቁ ለሱ ብቻ ሁል ጊዜ ተከታታይ ሰአት ተሰጠው ፣ ተሜ ሆይና መቸም ገና ከልጅነታችን ወሬ አፈንፋኝ
ነበርን ጋሽ አቤ ማመልከቻ ሲያስገባም ማመልከቻውን ሲያፀድቁለትም ቀድመን ሰምተናል ስለዚህ አዲስ በጠየቀው ፕሮግራም መሰረት የጋሽ
አቤ ክላስ ሁል ጊዜ እሮብና አርብ ከ 4፡00 ሰአት እስከ 6፡00 ሰአት መጀመሪያ አማርኛን ከዛ እስፖርት ክፍለጊዜውን ይቀጥላል
፣ ተማሪው ማልጎምጎም ጀመረ ‹‹ከጋሽ አቤ ጋራ በተከታታይ ሁለት ሰአት ልንቆይ እንዴኤኤኤ…›› ….ተልባ ቢንጫጫ ሁኖ ቀረ እንጂ
ምንም አላመጣንም፡፡ አርብ እና እሮብ ፆመኛ ነኝ እሚለው በዛ ፣ አርብ ጁማ ነው እሚለው በዛ ፣ ምድረ ሱሰኛም የመጀመሪያውን ፔረድ
እየፎረፈ እሚቀማምሰውን ቀምሶ ነቃ ብሎ በግድ የጋሽ አቤን ክፍለ ጊዜ ለመታደም ወሰነ፡፡
የሆነ ቀን እሮብ እለት ያው እንደተለመደው በመጀመሪያ
አማርኛ አስተምሮን ጨርሶ ወደሚቀጥለው የእስፖርት ክፍለ ጊዜ እንቀጥላለን አለና ‹‹እዚሁ ክፍል ውስጥ እናርገው ወይስ ዱብ ዱብ
ይሁን?›› አለን ፣ ዱብ ዱብ እሚላት ቋንቋ ስፖርት እንስራ ወይ ለማለት ነው፣ እኛ ባልነውማ ከሆነ ብለን በልባችን ‹እረ ጋሼ
ዱብ ዱብ ይሁን አልን› …በዛውም እኮ ለመሮጥና ለመዝናናት ስለፈለግን እንጂ እስፖርቱንም ወደነው አይደለም፡፡ አጅሬው ታዲያ አይ
ጋሽ አቤ ቸር አይደለ ‹‹እሺ›› ብሎ ‹‹በዚሁ ክላስ ውስጥ እንጨርሳለን›› ብሎን ቁጭ …በቃ ምን ታመጣላችሁ ነው ነገሩ ፣ ደሞ
እኮ እሚገርመው የኛን ፍላጎት እንደሚያሟላ ‹‹የቱ ይሻላችኋል?›› ብሎ መጠየቁ፡፡ ‹‹ስለ ፑሽ አፕ ፅንሰ ሀሳብ እንማራለን ዛሬ››
አለና ፊት ለፊት ወንበር መቀመጥ እወድ ስለነበር ‹‹እንካ ጥቁር ሰሌዳውን አጥፋልኝ›› ብሎ በቀኝ እጁ የያዘውን ዳስተር ወይንም
ማጥፊያ አቀበለኝ፡ ታዲያ ሁሉም ተማሪ ምን ነካው ዛሬ ብሎ ከኔ ጭምር አልጎመጎምን ፣ ያልጎመጎምነው ለምን በዛው ክፍለጊዜው ቀጠለ
ብለን አልነበረም ፣ ጋሽ አቤ ዛሬ እንዴት ዘነበን መጥራት ትቶ ብላክቦርዱን በኔ ማስጠፋት ወደደ ብለን ነበር የተገረምነው ፣ ዘነበ
ማለት በቃ የክፍላችን ብቅል አውራጅ አይነት ነገር በጣአአም ረጅእእእም ነው ፣ እርግጠኛ ነኝ ለሱ እሚሆን ሜትር ጠፍቶ አልተለካ
እንደው እንጂ ከአለም ረጅሙ ሰው ዘኔ ሳይሆን አይቀርም ፣ እንደውም እኔ ስገምት በጣም በመርዘሙ የተነሳ ሰማይና ዳመናውን በቴስታ
እየመታ ዝናብ ስለሚያወርድ ሊሆን ይችላል ዝናቡ ያሉት ፣ እኔ ደግሞ በተቃራኒው የአጭር አጭር ነኝ ያው ዘነበ በኔ ቢሰላ እኔን
አንድ አስር አይሆንም ብላችሁ ነው ፣ ታዲያ ተማሪውን ያስገረመው እኔን የመሰለ ሸበላ ድንክ ከብላክቦርዱ ግርጌ በግድ እምደርስ
ልጅ ለምን ተነስ አጥፋ አለኝ ሳስበው ለራሴው ዘገነነኝ አልደርስሰ ብዬ እንጣጥ ባልኩ ቁጥር ተማሪው በሳቅ ይፈርሳል ፣
ጋሽ አቤ አፍጥጦ ያየኛል ፣ አይቶ አይቶ ታዲያ ‹‹አያችሁ
ከዚህ ልጅ ምን ተማራችሁ እስቲ?›› ብሎ ጠየቀ…
አንዱ እጁን አወጣና ‹‹ ያላቅም መንጠራራትን›› አለ
ሌላኛው አወጣና ‹‹አጭር የመሆን ጉዳትን›› …ወደ ሌላ ሶስተኛ ተማሪ እጅ ሲመለከት የሆነች ሴት ልጅ ድምፅ ተሰማኝ ይህች ልጅ
በነገራችን ላይ የብርጓል ትባላለች ፣ ጋሽ አቤ ደግሞ እዚች ልጅ ላይ በመከየፉ ብዙ ልጆች እሱ ሳይሰማ ሙድ ይዘውበታል ፣ አሷንም
አላስኬድ አላስቀምጥ በለዋታል፣ ጋሽ አቤ ታዲያ ሲጠራት የብርጌ ብሎ ነው ፣ ‹‹እሺ የብርጌ ምን ተማርሽ ከዚህ ልጅ›› አላት
..ወይኔ ዛሬ የማንም መጠቋቆሚያ ያርገኝ እንደዛሬው ትልቅ ብሆን ኑሮማ በሞራሌ ላይ ተረማመደ ብዬ ፍርድ ቤት ነበር እምገትረው
፣ ታድሎ የዱሮ ዘመን አስተማሪ ሁኖ አልፏል ፣ በዚህ ዘመን አይደለም የሀይስኩል ተማሪን ይቅርና አንደኛ ክፍል ተማሪን እንኳን
ማንጓጠጥ ክልክል ነው፡፡
‹‹እሺ እኔ የተማርኩት›› ብላ ቀጠለች ወይ ጣጣ ደሞ
ምን ልትል ነው ይች ብዬ ለፍርድ እንደቀረበ ወንጀለኛ ተማሪዎቹ ፊትለፊት ቁልጭ ቁልጭ እላለሁ ፣ ‹‹እ….እኔ የተማርኩት እንዴት…አጭር
ሰዎችም ብላክቦርድ ማጥፋት እንደሚመኙ እና ›› እንዳለች ገና ሳትጨርስ ‹‹በትክክል በትክክል ቀጥይ የብርጌ›› አላት በታላቅ ሞራልና
ድጋፍ ፣ ከዛ እሷም ደረቷን ነፍታ ፀጉሯን ወዲያና ወዲህ እያዛነፈች ቀጠለች እየተሞላቀቀች ‹‹እና ይህ አጭርዬ ልጅ ቢያንስ የታችኛውን
የብላክቦርዱን ግርጌ ጠርዝ ጠርዙን ነገር መወልወል እንደሚችል እንዲሁም ሌሎች አጭርዬ (ወይ ጣጣ አጭርዬ ቆይ ቁልምጫ መሆኑ ነው
ድንቄም) ልጆች ከሱ እንደሚማሩ ተምሪያለሁ…ሁ››
‹‹ግባ ተቀመጥ እዛ….››አለኝ ጋሽ አቤ በጣም ተናዶ
፣ እንዴ ቆይ እስቲ ምን አናደደው ፣ በኔ ነው የተናደደው ወይስ በተማሪዎቹ የእውነት ያኔ በኔ ከሆነ የተናደደው እስከዛሬም ያናደኛል
፣ አጭር በመሆኔ ከተናደደ በጣም ነው የሚያስቀው አልኩ ለራሴ በሀሳብ ፣ እንዴ እኔ አጭርነቴን ጥሬ ግሬ ያመጣሁት መሰለው እንዴ
፣ ወድጄና ፈቅጄ ልሁን ብዬ የመረጥኩት መሰለው እንዴ ውስጤ በንዴት አረረ፡፡ ‹‹ቆይ እናንተ አህዬች ፣ እበት ›› ብሎ በንዴት
መጀመሪያ ላይ ከሴቷ በፊት እጅ አውጥተው ወደተናገሩት ወንዶች ልጆች አይኑን አጉረጠረጠ ‹‹ያላቅሙ መንጠራራትን …እ…አጭር የመሆን
ጉዳትን ነው የተማርነው ትላላችሁ አፍ አለን ማሰቢያ ጭንቅላት አለን ብላችሁ እ…አናንተ ውሾች›› ስድቡ በቃ ለነገ አያስቀምጥም
ከመጣበት እንዲህ ነው ጋሽ አቤ፡፡
‹‹ለማንኛውም ከዚህ ልጅ የተማርነው እና ልንማር የምንችለው
ነገር ቢኖር›› ብሎ ቀጠለ ‹‹ቅድም የብርጌ እንዳስቀመጠችው ›› ብሎ ‹‹ያንቺ እንዳለ ሁኖ የብርጌ ለመጨመር ያህል ይህ ልጅ አልሸነፍ
ባይነትን ፣ ወደ ላይ ጫፍ የመድረስ የማደግ ምኞትን ፣ አልችልም አለማለትን ነው የተማርንበት ፣ ብላክቦርዱ ላይ ወደ ላይ ሲዘል
ቅድም ልብ ብላችኋል አይደል?›› ብሎ ሲጠይቅ ይሄ እርጉም ተማሪ ሁሉ አውቀው ዝም አሉ ፣
‹‹ና እስቲ አሳያቸው ጎሽ›› አለኝ ምኑን ጋሼ ስል ‹‹የቅድሙን
አዘላለክን ነዋ ስለምነንድን ነው እያወራሁ ያለሁት አንተ›› ብሎ አንባረቀብኝ ፣ ወይ ጣጣ ይሄ ሰውዬ አበደ እንዴ ዝም ብሎ በቃ
እቃቃ መጫወቻ አረገኝ እኮ….ወጣሁና እንጣጥ እንጣጥ ብዬ ተመለስኩ ፣ እናመሰግናለን በል ግባ አለኝ መልሶ…‹‹ይሄን እንጣጥ እንጣጥ
ነው እንግዲህ ልንማርበት ይገባል ያልኩት›› አለና ጋሽ አቤ ወደዛሬው ክፍለጊዜያችን ገባ እስፖርት ስለ ፑሽ አፕ ነው የምንማረው
‹‹በመጀመሪያ እስቲ ፑሽ አፕ ምንድን ነው የሚነግረኝ?›› አለ ፣ የብርጌ እጇን አወጣች ‹‹እዚጋ ቲቸር ›› አለች በነገራችን
ላይ ቲቸር በማለት የምትጠራው እሷ ብቻ ነች የሆነች ሞልቃቃ ነገር ነች ሌሎቻችን በሙሉ አጎታችን ይመስል አቤን ጋሽ አቤ እያልን
ነው የምንጠራው ፣ ለዛም ይመስለኛል ታዲያ ለጋሽ አቤ የብርጓል ብቻ ናት ተማሪ የምትመስለው በቃ በእንግሊዝኛ ቲቸር ትለዋለች ፣
ሞልቃቃ ነች ፣ ደበተሮቿና ቦርሳዋ ከሌሎቹ ሁሉ ይለያል ፣ ኩሩ ነገር ናት ፣ እንደኛ በእረፍት ሰአት ተጋፍታ ጮርናቄ አትበላም
ይሄ ሁሉ ባህሪዋ ታዲያ የጋሽ አቤን ቀልብ ገዝቶታል፡፡
የብርጌ በዛ ሞልቃቃ አፏ ‹‹እ..ዚ..ጋ ቲቸር ፑሽ አፕ
ማለት …የሆነ የፊት እጆቻች..ንን ወደመሬት ተክለን ወደላይ ወደታች እንዲህ እንዲህ ማለት አይነት እስፖርት ነው›› አለች እንዲህ
እንዲህ እሚለውን እራሷን ቁልቁል እየወዘወዘች አሳየችው ለጋሽ አቤ ከዛ እንደተለመደው ከአፏ ላይ ተቀብሎ ‹‹በጣም ጎበዝ የብርጌ
excellent ደሞ በተግባር ለመግለፅ የሞከርሽው ሙከራ ተመችቶኛል›› ‹‹ምናባቱ ሆናችሁ ነው እስቲ እናንተ እጅ ስታወጡ የነበረው
፣ ደህና ሀሳብ ያላችሁ አትመስሉም እስቲ ስትንጋጉ ደሁ ሁላ እዚህ ደሞ በስርአቱ አውጡ እስቲ እጅ ስታወጡ ፣ አታዩአትም የብርጌን
እጅ አወጣጥ አነጋገር ስርአቷ!›› ዘወር ዘወር ብለን ተያየን ፣ ተጎሻሸምን፡፡
‹‹ፑሽ አፕ አያችሁ ቅኔ ነው ፣ ቅድም በአማርኛ ክፈለጊዜያችን
ስለቅኔ ምንነት አይተናል አይደለም ፣ አንድም ሰውነት ክፍ ዝቅ ሲል ስለሚጠነክር ስፖርት ይሆናል በሌላ በኩል ደግሞ የህይወትን
ውጣ ውረድ እ…የህይወትን ከፍ ዝቅ እምንማርበት ነው አያችሁ ፑሽ አፕ ቅኔ ነው እ›› ሲል ጋሽ አቤ ሳቄ መጣ አሁንስ አበዛው እንደው
ዝም ብሎ የመሰለውን ከማይመስለው ጋር እየቀላቀለ ማስተማር ጀመረ ፣ ካሁን በፊት እንዲሁ በማይመስል የማስተማር ክህሎቱ ብንገመግመው
ይባሱኑ ጥርስ ውስጥ አስገባን ውይ ውይ ውይ ጋሽ አቤ ብሎ አስተማሪ……
ሌላውና በጣም የሚያስቀው ባህሪው ጋሽ አቤ ከልጆች ጋር
ማውራት መጫወት ነው እሚወደው ትልቅ አኩያ ጓደኞች የሉትም ኳስ ስንጫወት አብሮ ይጫወታል ፣ ቺክ አቁመን ስናናግር ካየ ‹‹ቆይ
እስቲ ነይ በላት አንተ ፣ አስተማሪያችሁ እንደሆንኩ ነግረህ ለምን አታስተዋውቀኝም እረ ተው ተው አንተ ልጅ ነግሬሀለው ›› እንዴ
ጋሼ ለአንተ እኮ አትሆንም ምናምን ማለት አይቻልም እሱ ጋ፣ የሆነ ቀን ከሌላ ትምህርት ቤት ጋር ለውድድር ኳስ ስንጫወት አስቡት
ተማሪ ለተማሪ ነው ውድድሩ ማለትም አስተማሪን አያካትም ወይንም ተማሪና አስተማሪ ተዳቅሎ አብሮ መግባት አይችልም እሱ ግን በፍፁም
እምቢ ብሎ ገባ ተማሪ ነው አንል ነገር ግዙፍነቱ ፣ ሽበቱ በአጠቃላይ ቅድመ አያታችን የሚመስልን ሰውዬ እንዴት ከለጋ ተማሪ ጋር
ተማሪ ነው እንበል ፣ ዳይሬክተሩ ቢቆጣው ፣ በዘመድ ቢመከር ፣ ዳኞች ተው እባክህ ቢሉት እረ በጭራሽ ‹‹ወይ እኔ ት/ቤቱን እለቃለሁ
ወይ ውድድሩ ይቆማል›› ብሎ ገገመ ፣ ከዛ በቃ ይጫወት ተብሎ ጋሽ አቤ በአማካይ ቦታ በነገራችን ሲጫወት በቃ የያኔው ዣቪ በሉት
ምርጥ አከፋፋይ ነው መሀል ላይ ሌላ ተማሪ ቀነስንና ጋሽ አቤ በቡድኑ ውስጥ ተካተተ፡፡
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ያው መቸም የቡድኑ አንበል ብቻ
ሳይሆን አባታችን ነው ጋሽ አቤ ፣ ሰበሰበንና ታዲያ ምን ቢል ጥሩ ነው ‹‹እየው እያንዳንድሽ የትኛውንም ኳስ በንከኪ ነው የምትጫወቱት
ይሄ ዝም ብሎ እጠልዛለው ምናምን እጠልዝሀለው ፣ እያንዳንዷ የኳስ ንክኪ ታዲያ ከኔ ነው የሚጀምረው ፣ ተመልከቱ ብሎ እንዳሰልጣኝ
ማስመር ጀመረ ›› በለው ፈርጊ አለ አንድ ዱሬዬ ተማሪ ‹‹መጀመሪያ በረኛ ለተከላካይ ተከላካይ ለአማካይ አማካዩ ያው እኔ ነኝ
እኔ ካሰኘኝ እራሴ አብዶ ሰርቼ አገባዋለሁ ካላሰኘኝ እኔ ለአጥቂ አቀብላለሁ›› ወይኔኤኤ ጉዴ በቃ ምኑን ኳስ ነካሁት አለ አንድ
የተማመንበት አጥቂ ተጫዋቻችን ‹‹ሰማችሁ አይደለም›› አለ በቁጣ አዎ አልን፡፡
ከትንሽ ሰአት በኋላ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ጨዋታ ተጀመረ
፣ ስንቶቹ ፍሬንዶች ቺካቸው ፊት አብዶ ምናምን ሲከውኑ ለመታየት የተዘጋጁለት ጨወታ እድሜ ጋሽ አቤ ለሚባል ደንቀራ አስተማሪ አላማችን
ሁሉ ፉርሽ ሆነ ፣ እዛ ት/ቤት እኮ ሆነን እድሜ ለጋሽ አቤ እንደ ልጅነታችን ሳንቦርቅ ሳንጫወት ፣ እሱ እኮ እቃቃም ብንደረድር
አብሬ እጫወታለሁ እሚል ጉድ ነው ውይ ውይ ውይ……
የመሀል ዳኛው ፊሽካ ነፉ ተጀመረ ጨዋታው ሜዳ ውስጥ የመጡት
የሌላው ት/ቤት ደጋፊዎች አንዳች ለፊታቸው አዲስ ነገር አዩ ሜዳ ውስጥ ፣ የሆነ አውሬ የገባ የሆነ ባእድ ነገር የተቀላቀለ ይመስል
‹‹ምንድን ነው መሀል ላይ ጉብ ያለው›› እማይል ሰው የለም ‹‹….እንዴኤኤ..ጭራሽ አብሮ ይጫወታል እንዴ›› እማይል ሰው አልነበረም፣
ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጋሽ አቤ በነገረን ቀመር ተጫወትን ፣ ከዛ በኋላ ግን የጎል ናዳ ዘነበብን ፣ ለምን ቢባል ለጋሽ አቤ እናቀብላለን
ብለን ፣ አንድ የቡድናችን አጥቂ የነበረ ልጅ ለምሳሌ ጎል ስር ከደረሰ በኋላ መልሶ ስንት ሰው አልፎ…አልፎ….ጋሽ አቤን ፍለጋ
ተንከራትቶ…..ተንከራትቶ….(እኔ ክርትት ልበል እንዴት እንዳሳዘነኝ ) ቆሞ ሲያይ ጋሽ አቤ ውሀ ሊጠጣ ዳር ቆሟል ፣ እዛው ሆኖ
ታዲያ ጋሽ አቤ ‹‹መጣሁ መጣሁ ለሌላ እንዳታቀብል ›› ሲል ሰማሁት ምን አይነት ሱስ ነው ዘመዶቼ….